የትህነግን ነርቭ የነካው የአዳነች ንግግር

ክንፉ አሰፋ

 

          ሰሞነኛው ዶፍ ደግሞ ገራሚ ነው። ከትህነግ ጎራ ፤ ሳር እና ቅጠሉ ሳይቀር በአንድ ድምጽ እየጮኸ ሙሾ መውረዱን ታያይዞታል።  ስስ ብልቱ ሲነካ፣  የነርቭ ማዕከሉን መናጋቱንም ይነግረናል – ክስተቱ።

 

          እንገነጠላለን ብሎ የተናገረው መሪያቸው ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል እንጂ ከንቲባ አዳነጭ አቤቤ አይደሉም። “የትግራይን ህዝብ መፃኢ ዕድል ለመወሰን ህዝበ ውሳኔ እናደርጋለን” በሚል ቃል ቀባብቶ ያቅርበው እንጂ ትርጉሙ ግን ያው ስልቻ ቀልቀሎ ነው።   ኮሚኩ ስታሊን ደግሞ በቴለቪዥናቸው ላይ ወጥቶ “ተገንጥለን የትም አንሄድም። ወዴት ነው የምንሄደው?” በሚል ሳውንድ ትራክ ሳንወድድ እንድንስቅ አድርጎናል። ጥርሴስ ልማዱ ነው ሆዴን አታስቀው እንዲሉ፣  የውሸቱ ፋብሪካ በዚህ አይነት ወግ ሲመጣ ህዝበ አዳም በሳቅ ባይፈርስ ነው ነው የሚገርመው። ጅሉ ሞሮ በየእለቱ እየቀረበ የሚቀልድበት ይህ ቻናል አሁን ላይ እንደ የፈጠራ ምንጭ ሳይሆን እንደ መዝናኛ የሚደበሩበት ሆኗል።  ይህ ልጅ ደም-ስሮቹ እስኪገታተሩ ድረስ የ“አንገነጠልም” መፈክር እንዲያሰማ የገፋው ነገር የከንቲባ አዳንች ንግግር መሆኑ ግን ብዙ ያስብላል።   

 

          “አንቺው ታመጪው፣ አንቺው ታሮጪው” አለ የሃገሬ ሰው። አይ መሬት ላይ ያለ ሰው!  መቼም ወዶ አይስቅም። እንገንጠል እያሉ ሌት ተቀን የሚያደነቁሩን እነሱ፣ መገንጠል አንፈልግም በሚል የሚጮሁትም እነሱ። አይናችንን እያየ እድገታቸው ቁልቁል ወርዶ ወደ ሕጻንነት መቀየሩን ግን ያስተውሏል። እናንተ ካላችሁን እንደውም ትተነዋል አይነት ነው። የማይፈልጉትን ነገር እንዲፈልጉት ለማድረግ መፍትሄው ከነሱ በተቃርኖ መናገር ኖሯል!

 

          አንዳንዶች ደግሞ በአናቱ ላይ ቀጠን ያለች መስፈርት ጨምረውበታል። የምንገነጠለው ኢትዮጵያ የምትባለዋን ሃገር ከበተንን በኋላ ነው – በማለት።       በዚያም ላይ የሚወራረድ ሂሳብ እንዳለ ደብረጺዎን መተንፈሳቸው የግንጠላ ድራማውን ውስብስብ አድርጎታል። ካሳ መጠየቃቸው እንጂ መገንጠል የምትለዋን ጨዋታ  መጀመራቸውን የሚያመላክቱ ድምጾች መሰማት ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል። አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብሎ የትግራይን ግንጠላ ለማብሰር ተጣድፈው የነበሩትን ሰዎች እዚህ ላይ ማንሳቱ ፋይዳ የለውም።

 

          እርግጥ ሰዎቹን በዚህ ልክ ያንጨረጨራቸው የወ/ሮ አዳነች አቤቤ ንግግር ነው ወይ ብሎ መጠየቁ ግን ተገቢ ነው። ከንቲባዋ አዲስ እና ከዚህ ቀደም ያልተደነሳ ነገር አላነሱም። “ከጦርነቱም በፊት ከፈለጉ ትግራይን መገንጠል እንደሚችሉ ነግረናቸው ነበር።  አሁንም ከፈለጉ ትግራይን ይገንጥሉ እንጂ ኢትዮጵያን የማፍረስ ስራ ውስጥ ለምን ይገባሉ?” የሚል ምክር ነው የሰጡት።   ትግራይን ሃገር ለማድረግ ካስፈለገ ኢትዮጵያን ማፍረስ አያስፈልግም። ህዝቡም ከኢትዮጵያ መገንጠል እፈልጋለሁ ከለ ትህነግ ራሱ የጻፈውን የህገ-መንግስት አንቀጽ ጠቅሶ በዚያ መሰረት መሄድ ነው።  

 

            ከንቲባዋ “ትግራይን መገንጠል አይቻልም!” ቢሎ ኖሮስ አዋራው በዚህ መጠን ይነሳል ወይ ብለን ደግሞ እንጠይቅ።   መብታችንን የሚጋፋ ሃሳብ ተብሎ የመድረካቸው ማሞቅያ ከመሆን አያልፍም ነበር።  መገንጠል ህገ መንግስታዊ መብታችሁ ነው ማለት በዚያ መጠን ካስጮኻቸው፣ የዚህ ተቃራኒ ሃሳብ ቢነሳ ምን ሊሉ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም። ለፖለቲካ ትክክለኛነት እየተባለ ቃል ተመርጦ እና ተቀባብቶ ስለሚነገር እንጂ፣ የአዳነች ንግግር የቃላት ስንጠቃ የማይወጣበት ግልጽ የሆነ ሃሳብ ነው።  

 

          ፖለቲካውን ለማሳመር በሚል እሳቤና በይሉንታ ይነገር ይሆናል እንጂ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ላይ ያለውን ሃሳብ ቢጠየቅ ከከንቲባ አዳነች የተለየ ሃሳብ ሊሰጥ አይችልም። ምክንያቱም እነሱ ያነሱት የመብት ጉዳይ ነው። መንትህን መጠየቅ የለብህም ማለት አይቻልም።          እርግጥ ደብረ ጺዎን ይህን ጥያቄ ያነሱት ከእልቂቱ በፊት ቢሆን ጥሩ ነበር።  አሁን ከረፈደ ሲያነሱም፣ ይሁን፤ አድርጉት ተባሉ። አራት ነጥብ።  ይህ ግልጽ እና ቀና ምላሽ በዚያ ልክ ለምን አፍጨረጨራቸው?  ሰመነኛው የሸገር ጽዳት ዘመቻ የዚህን ጥያቄ ምላሽ ይሰጠን ይሆናል።

 

          መሸገር ላይ የተጀመረው ብርበራው እና ምርመራ ለዚህ ሁሉ ጩከት ገፊ ምክንያት መሆኑን ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ማስባሉ አልቀረም። የአዲስ አበባ ነዋሪዎቼ ላይ ስጋት ናቸው ያለቻቸውን ሰርጎ-ገቦች መመንጠርዋ የሰዎቹን ደም እፉኛ ማፍላቱ ተስተውሏል። በወሎ ደሴ ላይ የተሰራው ድራማ በአዲስ አበባ የመደገሙ አዝማሚያ ፉርሽ ያደረገ ኦፐሬሽን። መዲናዋ ውስጥ ተቀበሮ የተገኘውን ገንዘብ፣ ወርቅ እና የጦር መሳርያ በአይኑ ለሚመለከት ከተማዋ ላይ ታቅዶ የነበረውን የጥፋት ክብደት እና መጠን ይገለጥለታል። ከላስቲክ ቤት እስከ ዘመናዊ ቪላ ተዘጋጅቶ የነበረው ትልቅ የጥፋት ድግስ እጅ በአፍ የሚያስጭን ነው። በፈጣሪ ብርታት ከሸፈ እንጂ፣ ሰዎቹ መዲናዋን ሞቃዲሾ ለማድረግ ረጂም መንገድ መጓዛቸውን በተግባር አሳይተዋል። አላማቸውን ከግብ ለማድረግ ተዋንያኑ የጎዳና ተዳዳሪ ገፀ-ባህርይን ሳይቀር መላበስም ነበረባቸው።  “አዲስ አበባ ከብዙ አመት ቆሻሻዋ እየጸዳች ነው።” የሚለው የአዳነች አቤቤ ንግግርም እንደ ቅኔ ነበር የተወደው። እቅዱን ከስረ መሰረቱ የሚያውቀው ቡድን ደግሞ የዚህን ቅኔ ሰም እና ወርቅ ማግኘት አልቸገረውም። ውጤቱ ምንም ይሁን፣ በከንቲባ አዳነች ላይ የተነሳው ጩኸት ምክንያቱ በአዲስ አበባ የተሸረበው ሴራ ጭራ መያዙ ነው።

 

          ጨዋታው የገባው ውሃ የማይቈጥረውን የትህነግ አመክንዮ ጠንቅቆ ይረዳዋል። እንጂ ግንጠላው እና የዴፋክቶ ስቴት ምስረታው ከተበሰረ አመታት አልፈዋል።  የትግራይ መንግስት፣ የትግራይ ሰራዊት፣ የትግራይ ወዘተ እያሉ ትግራይን በሃሳብ ከገነጠሉኮ ቆዩ። “ጉዳያችን ከሕዝቡ እንጂ ከመሬቱ አይደለም” የሚሉ የዋህ ፖለቲከኞችን ጭምር አንገት ካስደፉ ከረሙ። “እርስ በርስ የተጋባ እና የተዋለደ ሕዝብ፣ አብሮነት፣ ወንድማማችነት ወዘተ በሚል ዲስኩር የሚሞግት እንኳ መጥፋቱ በዚህ ምክንያት መስሎን።  አብሮነት፣ ወንድማማችነት ወዘተ የሚለው ዲስኩር ከሕዝብ ፍላጎት አይበልጥም። እነንተ ከፈለጋችሁ ሂዱ ማለት ታዲያ ሃጥያቱ ምኑ ላይ ነው?

 

          በዚያ ለስላሳ ቃል አሁንም የሚባትለው ክፍል እርግጥ ህዝቡን ብሎ እንጂ መሬቱማ ጭንጫ ድንጋይ መሆኑን አጥቶት አይደለም። አራት ሚሊዮን ሕዝብ በሴፍትኔት ማስተዳደር ምን ያህል እንደከበዳቸው በተግባር አሳይተዋል። በአናቱ ላይ መገንጠልን ሲጨምሩበት ደግሞ ነገሩ በእንንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑን ያውቁታል። ክልሉን ገንጥለው የትግራይ ህዝብ ችግርን ማብዛት ከሆን አላማቸው ግን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትህነግ ያተረፈው ጦርነትን እና ዝርፊያን ብቻ ነው።

 

          የአጠቃላይ ሕዝቡን እንጂ የትህነግን ሃሳብ ለማወቅ የፖለቲካ ሳይንቲስት መሆንን አይጠይቅም። አብዛኛው ትህነግ ኢትዮጵያዊነትን አልፈልግም እያለ በአደባባ ሲደነፋ ይሰማል። ብሄራዊ ባንዲራዋን እየረገጡ አብሮ መኖር ይከብዳል። ፎጣ ለባሽ፣  ሃድጊ እያሉ አብሮነት ሊኖር አይችልም።  በሰው ጓዳ ገብተው ሊጥ የሚሰርቁ እና  እንስሳ የሚረሽኑትን ዳግም በጫንቃው የሚሸከም ሕዝብ አይኖርም።

በእንገንጠል ድቤ ጆሯችንን ሲታደነቁር የነበረው ዲጅታል ወያኔዎች፣ “መገንጠል ፈቀዱልን” በምትለዋ አዲስ ዜማ የማህበራዊ ትስስሩን የማድመቃቸው ጉዳይ ግን ምክንያት አልባ ጉዳይ አይደለም። ስራዬ ብለው የያዙት የጦርነት ቢዝነስ ቀዝቀዝ ሲል ፖለቲካውን የማጦዙ ስትራቴጂ ነው። ማምሻም እድሜ ናትና የሚያነሱት ማዕበል ትንሽም ቢሆን ግዜ ለመግዛት ይጠቅማቸዋል።

 

          እርግጥ ህዝቡ ከፈቀደላቸው ትግራይን ልክ እንደ ዶሮ ብልት የመገንጠል መብት አላቸው። ይህች ጨዋታ ግን ፍላጎት ሳትሆን ማስፈራሪያ የመሆንዋ ምስጢር ለተገለጠለት ብቻ ነው። ዋና አላማቸው ግን ከዚያም ላቅ ይላል። እቅዳቸው ሀገርን ማፍረስ መሆኑን በተደጋጋሚ ነግረውናል።  እኛ የማንገዛት ሃገር ትበታተን በሚል መሪ ቃል። የፌደራሊስት ሃይሎቹ ምሶሶ ናት ያሉን ትግራይ፣ ምሶሶው ሲነሳ፣ የአዲሶቹ ኮንፌደራሊስቶች ቤት አብሮ ይፈርሳል ነው እሳቤው። ዛሬ የሚያለቅሰው የእንግዴ ልጅ በአንድ ወቅት በዚያው የትግራይ ጣቢያ ተከስቶ “ኢትዮጵያ በእኔ ዘመን መፍረሷን ከማየቴ በላይ ያስደሰተኝ ነገር የለም።” ማለቱን መቼም አንረሳውም።      

 

          አንቀፅ ሰላሳ ዘጠኝን በህገ መንግስቱ ለክፉ ቀን ብለው ያኖሩት ራሳቸው ናቸው። እርግጥ ሕዝቡ ከኢትዮጵያ ጋር ፍቺ ከፈቀደ ማንም ሊያስገድደው አይገባም።  ትግራይን ዱቄት ካደረጓት በኋላ ግን ይህ አንቀጽ ምቾት እንደማይሰጣቸው ግልጽ ነው። ራሳቸው በቆፈሯት ጉድጏድ ውስጥ ሊቀበሩበት እንደሆነ አሁን ላይ የባነኑም ይመስላል።  

 

          አንድ ትውልድን የቀጠፈ ጦርነት ውስጥ ከመግባት በፊት፣  የፍቺውን ህግ ጠቅሶ መሄድ አንድ ነገር ነው። ብለዋል ከንቲባዋ። አባባሉ ምንም አይነት የሞራልም ሆነ የፖለቲካ ስህተት  የለበትም። ንግግሩ በህግም የሚያስከብር እንጂ የሚያስጠይቅ አይደለም። አዳነች ሸገር ላይ ማድረግ የሚገባቸውን ነገር አድርገዋል። የፓለቲካውን ዜማ ያስቀየረ ጨዋታ።

 

          ፈጣሪ ኢትዮጵያን ከክፉ ይጠብቅልን