ጠረፋማ በሆኑ አካባቢዎች ሰርገው የገቡ የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች ተደመሰሱ | በርካቶችም ለጥፋት ከያዟቸው የጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል

ሀገር የማፍረስ እቅድ ይዞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠረፍማ አከባቢዎች ሰርገው የገቡ የአሸባሪው ህወሃት ተላላኪዎች ሲደመሰሱ ብዛት ያላቸው የጥፋት ታጣቂዎች ከያዙት የጦር መሳሪያ ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
አሸባሪዎቹን ለመደምሰስና በቁጥጥር ስር ለማዋል ህብረተሰቡ ለፀጥታ ሀይሎች መረጃ በመስጠት ቁልፍ ሚና እንደነበረው ተገልጸዋል።
የክልሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መምሪያ ዕዝ አብይ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሃመድ እንዳሉት፤ሰሞኑን እርምጃ የተወሰደባቸውና በቁጥጥር ስር የዋሉት የሽብር ቡድን አባላት፣በክልሉ ጠረፋማ አካባቢ በአሶሳ ዞን ኩርሙክ፣ ሸርቆሌ እና መንጌ ወረዳዎች የገቡ ናቸው።
ከተደመሰሱት መካከል በጎረቤት ሀገር ስልጠና ወስደው ወደ ክልሉ የገቡና እራሱን ቤህነን ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን አርማ የያዙ እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉትም ውስጥ የሰብዓዊ መብት ተቋም በሚል መታወቂያ የያዙ ግለሰቦች እንዳሉበት ጠቁመዋል፡፡
የአሸባሪው ህወሃት ተላላኪ ከሆኑት እነዚህ ግለሰቦች ጋር ክላሽንኮቭ ጠብ መንጃዎች ከመሰል ተተኳሽ ጥይቶች፣ “አርፒጂ” መሳሪያ ፣ ጸረ-ሰው እና ተሸከርካሪ ፈንጂዎች፣ የእጅ ቦምቦች፣ መገናኛ ሬዲዮኖች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና የጦር ሜዳ መነጽሮችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል።
ብዛት ያለው የሱዳን ፓውንድ፣ የሱዳን ጦር ዩኒፎርሞች እና ሌሎችም በጸጥታ ሃይሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል፡፡
ከህወሓት ጋር በማበር ሽብር እየፈፀሙ ያሉ የጥፋት ቡድኖች ዓላማ ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን ህዝቡ ሊረዳው ይገባል ያሉት ኮሚሽር አብዱልአዚም፤ ከጥፋቱ ጀርባ የአሸባሪው ህወሃት እና ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚጥሩ የውጭ አካላት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ እና መንግስት የአገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በየደረጃው በሚገኙ አካላት በቅንጅት ባደረጉት ኦፕሬሽን የአሸባሪው ተላላኪዎችን በመደምሰስ የጥፋት እቅዳቸውን ማክሸፍ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የተደመሰሱት እና በቁጥጥር ስር የዋሉት የአሸባሪው ህወሃት ጥፋት አስፈጻሚዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋልና ለመደምሰስ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት ቁልፍ ሚና መጫወቱን የመከላከያ ምንጮቻችን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
የመከላከያ ምንጮቻችን እንዳሉት፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የጸጥታ አስከባሪ ሃይሎች በቁርጠኝት ድጋፍ ማድጋቸውን ጠቁመው ይህም ቡድኑ እንዲደመሰስ ከፍተኛ አቅም ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ሠራዊቱ በየቦታው የተበተነውን የጥፋት ቡድን ርዝራዦች አድኖ የመደምሰስ ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል፡፡
የክልሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መምሪያ ዕዝ አብይ ኮሚቴ አባልና የሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ በበኩላቸው፤ የተደመሰሱ የጥፋት ተላላኪዎች ትኩረት ያደረጉት ንጹሃን ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የጥፋት ቡድኑን ከአካባቢው ሙሉ በሙሉ ለማጽዳት የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ እና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።