የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የኮረና መድሀኒት አግኝተናል ወሬ አላማው ምንድነው? – ሰርፀ ደስታ

ይሄን ዜና እየሰማን ያለንው የኢኖቬሽንና የጤና ጥበቃ ሚኒስተሮች በጋራ በወጡት መረጃ ነው፡፡ በብዙ ሰዎች ይሄው ወሬ ሲሰራጭ እያየወሁ ነኝ፡፡ በስልኬ ሳይቀር ሲመጡ የነበሩ መልዕክቶች ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ ጥሩ ነገር አይመስለኝም፡፡ በወሬ እንደልብ እንደምንዘወር ስለታወቀ ማንም የፈለገውን ለማውራትና ትኩረት ለማግኘት ማሰብ አያስፈለገው አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሆይ አባካችሁ አስተውሉ!

የባሕል መድሀኒቶች በእርግጥም ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው እናውቃለን፡፡ በቅርቡ በዓለም ላይ የኮረናን ቫይረስ ለማከም ምርምር እየተደረገባቸው ካሉ መድሀኒቶች አንዱ በቀጥታ የቻይና የባህል መድሀኒት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ከዛም በላይ ለበሽታው ማከሚያነት ዛሬ ትልቅ ተስፋ ተሰጥቶት በሰፊው በሰዎች ላይ እየተሞከረ የሚገኘውና ለበርካታ ዓመታት ለወባ መድሀኒትነት የዋለው ክሎሮኪዊኒን መነሻው በመድሀኒትነት በደቡብና መካከለኛው አሜሪካ ደም ብለው ይታወቁ የነበሩ ሲንኮና በመባል የሚታወቁ የዛፍ ዝርያዎች የሚያመነጩት ኪዊኒን የተባለ ንጥረነገር ነው፡፡ ዛሬ በአገራችን የመድሀኒት አንክብል ሁሉ ኪኒን የተባለውም ከዚህ ስም ተነስቶ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ኪዊኒን (ዘመናዊው ክሎሮኪዊኒን) በእርግጥም ለብዙ በሽታዎች ሕክምና ይውላል፡፡ ዛፎቹም በብዙዎች ዘንደ እንደ ነፍስ አዳኝ ስጦታዎች እንደሆ ይነገርላቸዋል፡፡ ይሄን ሁሉ የምለው የባህል መድሀኒቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው ወደ ዘመናዊነት ቢቀየሩ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ለመጠቆም ነው፡፡ ሲጀምር ብዙው መድሀኒት ቀደም ብሎ ከታወቁ የባሕል መድሀኒቶች ነው የሚቀመሙት፡፡ ልዩነቱ በባህል ፈዋሽ ንጥረ ነገር የሆነውን ብቻ ለይቶ አለመሰጠቱ ነው፡፡ በዘመናዊ መልኩ ግን ፈዋሽ ብቻ የሆነው ንጥረ ነገር በመለየት ስኬታማ መድሀኒት መስራት ስለሚቻል ነው፡፡ የኢትዮጵያ የባሕል መድሀኒቶችም ከዚህ አንጻር በምርምር በታገዘ ወደ ዘመናዊ መድሀኒትነት ለመቀየር ጥረት ማድረግ እንደውም ብዙ ዘመን የዘገየ በመሆኑ አዝናለሁ፡፡ አሁንም እንዲህ ያለ ጥረት መኖሩ አጠያያቂ ነው፡፡

ሰሞኑን የኮረናን ቫይረስ አስመልክቶ በአገራችን የሚሰሙ ብዙ ነገሮች ዓላማቸው ምን እንደሆነ ግልጽ አደለም፡፡ በቀደም በየኔታ ሚዲያ አንዱ ሰው እንዲሁ በባሕል መድሀኒት የኮረናን ቫይረስ ለማዳን ፎርሙለው አለኝ ሲሉ በድፍረት ነበር፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን እሳቸውም ሆኖ ሌላ የኢትዮጵያ ባሕል መድሀኒት አዋቂ ከዚህ በፊት በአገራችን አዲስ ኮቪድ19 የተባለውን በሽታ የሚያመጣውን ኮረና ቫይረስ አክመው ተሳክቶላቸው አያውቅም፡፡ ከዛ በዘለለ ግን ግለሰቡ ስለቫይረስ ያላቸው ግንዛቤ ራሱ ከውሱንም በታች ይመስላል፡፡ ምን አልባትም ጉንፋንንም ጠንቅቀው ላያውቁት ይችላሉ፡፡

አሁን ደግሞ ይባስ የጤና ጥበቃና የኢኖቬሽንና ምርምር የሁለት ሚኒስቴር የመንግስት ተቋማት እንዲሁ ለኮረና ቫይረስ መድሀኒት በምርምር ከባህል መድሀኒት አግኝተን ወደ ምርት ሳይቀር ለመግባት እየሰሩ እንደሆነ እየነገሩን ስንሰማ ገርሞናል፡፡ ቆይተው እነዚሁ ሁለት ሚኒስቴር ባለስልጣናት የባሕል ሐኪም እንደሆኑ ከሚናገሩት ወ/ሮ አበበች ጋር ሆነው መጀመሪያ የሰጡትን ማስተካከያ የሚመስል መግለጫ አይሉት፣ ትምህርት ወይም ትዕይነት አሳዩን፡፡ በከፍተኛ የምርምር ባለሙያዎች ተጠንቶ ቢሉንም ከፍተኛ ተመራማሪ ከሆኑት አንዱንም አላሳዩንም፡፡ በመድረኩ ካየናቸው ከፍተኛ ተመራማሪ አሉ ከተባለ የባሕል ሀኪሟ ወ/ሮ አበበች ብቻ ናቸው፡፡ የኢኖቬሽን ተወካዩ እንኳንስ ሰለመድሀኒቶቹ ይቅርና ስለእጽዋትም ብዙ የሚያውቁ አይመስልም፡፡ በኢትዮጵያ ከ6-7 ሺ የሚሆኑ እጽዋት ዝርያ እንዳሉ ሰዎች ሲናገሩ የሰሙ እንጅ ያነበቡም አይመስለም፡፡ ሆኖም ከኢትዮጵያ አልፈውም እንዲሁ በዓለም ምን ያህል እጽዋት እንዳለ ሊነግሩን ሞክረዋል፡፡ በእሳቸው ግንዛቤ በዓለም ላይ ወደ 8ሺ የሚሆኑ የእጽዋት ዝርያ ሲኖሩ በኢትዮጵያ እስከ 7 ሺ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ማለት በዓለም ከሚገኙት ወደ 88 በመቶው/ፐርሰነት ገደማ በኢትዮጵያ ይገኛሉ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ባለስልጣኖች ስለሚናገሩት ነገር በማይጠየቁባትና አልፎም በተናገሩት ነገር የአምልኮት ያህል የሚያምናቸው ብዙ በበዛበት አገር እንዲህ ያለ ነገር መናገር ለተናጋሪዎች ምሁርነት/አዋቂነት እንጂ ኃላፊነት የለም፡፡ ለማንኛውም ተናጋሪውም ሌላውም ሕዝብ እንዲያውቅ በዓለም ላይ ከ390 ሺ በላይ ከፍተኛ/ቫስኩላር (ሥር፣ ቅጠል፣ ግንድ/ብር) ያላቸው እጽዋት ሲኖሩ በእርግጥም በኢትዮጵያ እስከ ወደ 6500 ገደማ የሚሆኑት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ቫዝኩላር ያልሆኑትን አይጨምርም፡፡ ለግንዛቤ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእጽዋት ዝርያ ክምችት ያለባት አገር ነች፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዳሎል (-116 ሜትር) እስከ ራስ ዳሸን (4620ሜ) ያለው የመሬት ከፍታ ከጋምቤላ እሰከ ሱማሌ ያለው የላቲቲውድ (ኬንትሮስ) ርቀት ለዚህ የኢትዮጵያ በእጽዋቱን ጨምሮ የሥነ ሕወት ክምችት (ብዝሀነት) ምክነያት ነው፡፡ በዛው ልክ ብዙ ለመድሀኒትነት የሚውሉ እጽዋቶች እንደሚኖሩ የጠበቃል፡፡

የሆነ ሆኖ በጤና ጥበቃና በኢኖቬሽን ሚኒስትሮች የተናገሩት የመድሂኒት ምርምር ሂደት ዓላማው ምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም (ነበገራችን ላይ ኢኖቬሽን ለምን እንደተባለ አይገባኝም ቃሉ እንኳን ለሕዝብ ለተማረም ግልጽ አይመስልም)፡፡ በመጀመሪያ እነሱ እንደሚሉት ያለ ምርምር ለማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ምቹ ነገር ለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ እነሱ የሚሉት አይነት ምርምር ለማካሄድ የተሟላ የላቦራቶሪና ሌሎች ተያያዥ መስፈርቶችን ይጠይቃል፡፡ የሙከራ እንሰሳ ጭምር እንደተጠቀሙ እየነገሩን ነው፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያለ ምርምር ለማድረግ ትልቅ እውቀትና ቀደም ብለው የተዘጋኙ ምቹ ሁኔታዎች አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ እንኳን ኖረው የኮረናን ቫይረስ ኢላማ ያደረገ ምርምር ለማድረግ ብዙ ቅድመሁኔታ ይጠይቃል፡፡ ኮረና በአይን የማይታይ ብቻም ሳይሆን ሕወት ያለው ነገር እንኳን አደለም፡፡ በአጠቃላይ ቫይረሶች ሕወት ካላቸው ነገሮች አይመደቡም፡፡ አይመገቡም በራሳቸው አይራቡም፡፡ ቫይረሶች በአጠቃላይ የመለዘር (ዲኤንኤ/አርኤንኤ) ቅንጣቶች ናቸው፡፡ ወደ ሰውነት ወይም ሌላ ሕይወት ያለው ነገር ውስጥ በመግባት የገቡበትን ሕወት ያለው ነገር መለዘር ስርዓት በመጠቀም የራሳቸውን መለዘር የሚያባዙ ከዛ ግን መለዘራቸውን መሸፈኛ በራሳቸው የሚሰሩ ነገሮች ናቸው፡፡ ያም በመሆኑ እንደ ባክቴሪያ ምግብ በማሳጣት ወይም ለሕወት የሚያስፈልገውን የሆነ ነገሩን በማሳጣት የሚሞቱ አደለም፡፡ ለዛ ነው የቫይረስ መድሀኒት ለማግኘት ብዙ ጊዜ ከባድ የሚሆነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግን አሁንም መድሀኒት ከእነጭርሱ ሊገኝላቸው አይችልም ማለት ማለት አደለም፡፡ ባሕላዊ መድሀኒቶች መድሀኒት ሊሆኑ የችላሉ፡፡ የጤናጥበቃውና የኢኖቬሽኑ መረጃ ችግሩ ሕዝብ አያውቅም በሚል ድፍረት መሰል ነገር ዓለም በስንት ታላላቅ ቤተሙከራዎች እስካሁንም ይሄ ብሎ መድሀኒት ያላገኘለትን በጣም አዲስ ባይረስ በከፍተኛ ምርምር አገኘሁ ማለት ላይ ነው፡፡ የሚሉትን ምርምር ለማካሄድ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የተዘጋጀ ላቦራቶሪም ሆነ ሌላ የምርምር እንስሳቶችን ጨምሮ ያለው የምርምር ተቋም ቢጠቅሱልን ጥሩ ነው፡፡ ተመራማሪዎቹን ጭምር፡፡ ሳይንስ በዘፈቀደ አይሰራም፡፡ ምርምር ማረጋገጫን ይጠይቃል፡፡

እንዲህ ያለ ሕዝብ አያውቅም የፈለግንውን ብንል በሚል ድፍረት በዚህ መልኩ መረጃን ለሕዝብ ማስተላለፍ ሀላፊነት ማጣት ብቻ ሳይሆን ሕዝብን ማደናገር ማድረግ የሚገባውንም ጥንቃቄ እንዳያደርግ ማዘናጋት ነው፡፡ በእርግጥ ነው ተናጋሪዎቹ ገበያ ይገኝበታል በሚል የተናገሩት ይመስላል፡፡ ይሄ አይነት ድፍረታዊ ነግግግር በብዙ ፖለቲካ ነክና በአገር ልማቶች ላይ ለዘመናት የተለመደ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ተመራማሪም መሆን መቻላቸው ሌላው ችግር ነው፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሌሎች ሌላ ወሬ እየደገሱበትና እየሞሉን ነው፡፡ አንዳንዶች መድሀኒት ለማግኘት እስከ አስር ዓመት ጊዜ ያስፈልጋል የሚል ምሁራዊ ባሉት የራሳቸው ወሬ ሕዝብ እየሞሉ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ስለምርምሩ ግንዛቤው ራሱ ያላቸው አይመስልም፡፡ ምርምሩን ለማካሄድ ሁኔታዎችን ለማሟላት በመንግስት ደረጃ ማሰብ ይቅርና፡፡ በተግባር ለመስራት ማሰብ እንኳን ያልቻሉትን ሲሉ የሰሙትን በሚዲያቸው ወጥተው እየተናገሩት መሆኑ ነው አደጋው፡፡ ዝግጅቱ ቢኖር ግን አንድን መድሀኒት ለማግኘት ወራቶች በቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ተከታታይ የሆነ ምርምሮችን በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕክምና ማዋል ይቻላል፡፡ በእርግጥ ነው የምርምር ሂደቶቹን ሁሉ ማለፍ አለበት፡፡ በተለይ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ማጥናት ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ያም ሆን እንዲህ ባለ ሁኔታ መሠረታዊ የተባለ የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው ከተረጋገጠ በኋላ በቀጥታ በሰዎች ላይ ጥቂት በጥቂቱ የሰዉን ቁጥር እየጨመሩ ከተሞከረ በኋላ ለመድኀኒትነት ይውላል፡፡ በባሕል ሕክምና ወቅትም የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው የሚያሳይ መረጃ ካለ ለዚሁ ምርምር በግብዓትነት ያገለግላል፡፡ ከዛም ባላይ የንጥረ ነገሮችን ኬሚካላዊ ይዘት ማጥናት ስለሚቻል ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎች በንጥረ ነገሩ ከሌሉ ወይም ወደ ሰውነት ሲገቡ ከሌላ ጋር በመሆን የሚፈጥሩት ጉዳት ከሌለ ለመድሀኒት የሚውሉበት ፍጥነት ይጨምራል፡፡ ዛሬ ዓለም እየታገለ ያለው ከክትባት በፊት የታመሙትን ለማከም የሚረዱ መድሀኒቶችንም ማግኘት ላይ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ብዙ ሄደዋል፡፡
ሌላው እንዲሁ ለቫይረስ መድሀኒት የለውም አይነት ወሬም ሲያወሩ የተሰሙ አሉ፡፡ ጸረ-ቫይረስ መድሀኒቶች በርካታ አሉ፡፡ እርግጥ ነው የቫይረስ ሕክምና በጣም አስቸጋሪ የሚያደርገው ከላይ የጠቀስኩት የቫይረስ ባሕሪ ነው፡፡ ጸረ-ቫይረስ ለኤአይቪ ጨምሮ ለብዙ ቫይረሶች ተሰርቷል፡፡ አንዳንዴም የአንዱ ለሌላው ይውላል፡፡ ለዛም ነው አሁን የኤችአይቪን ጨምሮ ሌሎች ለወባ የሚውሉ መድሀኒቶች ኮረናን ለማከም የሚውሉት፡፡ ሁሉም የፀረ-ቫይረስ ባሕሪ ስላላቸው፡፡ በነገራችን ላይ የወባ በሽታ ባክቴሪያም ቫይረስም አደለም፡፡ ፕላዝሞዲይም የተባለ ተውሳክ(ፐሮቶዙዋ) እንጂ፡፡ ይሄ ከባክቴሪያ ከፍ ያለ የስነሕይወት መዋቅር ያለው ጥገኛ ተውሳክ ነው፡፡ ደግሞ ነገ አንዱ ተነስቶ ቫይረስ በሚል እንዳይተነትን ስለሰጋሁ ነው ለወባ የሚውል መድሀኒት ለኮረና ዋለን ስለሰማ፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩላችሁ ኪዊኒን የተባለው ከሲኮና ዛፎች ቅርፊት ሥር የሚገኝ ንጥረ ነገር ለብዙ በሽታዎች ፈዋሽነት ይታወቃል፡፡ ምን አልባትም የአገራችን የበሀል መድሀኒት የሚባሉት እንደነፌጦ እንዲሁ ያለ ባህር ያለው ንጥረ ነገር ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እናም ኪዊኒን የወባን ጥገኛ ይገድላል፣ ቫይረስንም ከሰውነት የማጥፋት አቅም አለው፡፡ የቫይረስ መድሀኒት ለማግኘት ከባድ ነው እንጂ መድሀኒት ከእነጭርሱ የለም ማለት አደለም፡፡ አሁን አንዳንዶች እስሚቀጥሉት አራትና አምስት ወራት አዲስ መድሀኒት ለማድረስ ተስፋ እየሰጡ ነው፡፡ ነባሮቹን መድሀኒቶች ጥናትም በሰፊው እየተካሄደ ነው

ሌላው ስለ ክትባት ምሁር ሆነውም የተደመጡ አሉ፡፡ በእርግጥም በአሁኑ ጊዜ የኮረና ቫይረስ ክትባት በሙከራ ላይ ነው፡፡ በሰው ላይ ጭምር ማለት ነው፡፡ ክትባቱን የሰራው ድርጅት የኮረና ቫይረስን የመለዘር ረድፍ (ሲኩዌንስ) በቻይናዎች ከተለቀቀ ከሶስት ቀን በኋላ ነው፡፡ ይህ ክትባት በዓይነቱም ከዚህ በፊት ከነበሩት የተለየ ነው፡፡ በፊት የነበሩ ክትባቶች ለማጥቃት የማይችል ደካማ የማጥቃት ኃይል ያለውን ቫይረሱን ራሱ ወደሰውነት መማስገባት ሰውነት ለዚሁ ቫይረስ መከላከያ የሚሆን እንዲያመነጭ ማነቃቃት ነበር፡፡ አሁን በሰው ላይ ሙከራው የተጀመረው ክትባት ግን በቀጥታ ተላላኪ (ሚሴንጀር) አርኤንኤ በመጠቀም ነው፡፡ ሌሎች በርካታ የተለመደውን ክትባት እየሰሩ ያሉ አሉ፡፡ ክትባቱ ከስድስት ወር በላይ ሊያስጠብቅ ይችላል፡፡

እንግዲህ ኢትዮጵያ የዚሁ የአለም የመድሀኒት ምርምር ተሳታፊ መሆን የምትችልበት እድል እንዳለ አሳምሬ አዋቃለሁ፡፡ ሆኖም ከወዲሁ እንዲህ ባሉ የምርምሩን ሥራ በዋናነት በሚመሩ ሚኒስቴሮች በሚታሰበው ለወሬ የመሽቀዳደም አይነት መቼም እንዳይሳካ ሊያደርግ እንደሚችል እሰጋለሁ፡፡ ብዙ ነገሮቻችን በዚህ መልኩ ነው የጠፉት፡፡ ሳይንስ የሚባለው ነገር እኛ አገር የመፍትሄ ምንጭ ሳይሆን የምሁርነት መገለጫ ለማድረግ ታላላቅ ቃላቶችን በመናገር ሕዝብን ማደናገር ነው፡፡ ዓለም ያደገው በተግባር በሚተረጉሙ ምርምሮች ነው፡፡ አብዛኛው ምሁር ችግር ለማውራት እንጂ ለመፍትሄ ምርምር የሚባል ነገር ለማሰብ የደክማል፡፡ በወርክሾፕና በስብሰባ ሁሉን ነገር ይጨርሱታል፡፡ ሌሎች የሳይንሱ ጫፍ የደረሱ ለመናገር የማይደፍሩትን ምናባዊ ሳይንስ ለመናገር ብዙ ደፋሮች አሉን፡፡ ምክነያቱ ደግሞ መጠየቅ የለም፡፡ መለኪያ የለም፡፡ ማረጋገጫ የሚጠይቅ የለም፡፡ ሌላ ቀርቶ በተመራማሪነት ከሌሎች በኣለም ካሉ ጋር የሚያፎካክረውን የሳይንሳዊ ጥናት ውጤት በማሳተም ራስ መገምገም የለም፡፡ ማሳተም ብቻ ግን አሁን እንደምናወራው ያለ ምርምርን ለማድረግ በቂ አደለም፡፡ ለዚህ የተመረጡ የምርምር መጽሄቶች ላይ መውጣት ካልቻለ፡፡ በዚህ አጋጣሚ እንዲህ ያሉ ምርምሮችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚቻል ልጠቁም እወዳለሁ፡፡ ብዙ ማለት አለፈልግም በዚህ ጉዳይ ለጊዜው ግን ሕዝቡን በወሬ ባታዘናጉትና እላለሁ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ምህረቱን ለዓለም ሁሉ ይላክ! ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ