በፍሎሪዳ ታምፓ ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

‹‹በፍሎሪዳ በሚገኘው ታምፓ ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ›› ሲል ስፔክትረም ኒውስ ዛሬ ዘግቧል፡፡

እነዚህ በአስራዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተቃዋሚዎች በመንገዶች ላይ የኢትዮጵያንና የአሜሪካን ባንዲራ ሲያውለበልቡ እንደነበር ዘገባው ጨምሮ አስረድቷል፡፡ ዘገባው ይህን ይበል እንጂ የተመለከትነው የኦነግን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ነው፡፡ የተቃውሞው አስተባባሪ ኢማኑኤል በዳሶ ሲናገሩ ‹‹እኛ በታምፓ የምንገኝ ሰዎች ትንሽም ብንሆን በአገር ቤት ካሉ ወገኖቻችን ጎን መቆማችንን ለማሳየት ፈልገናል፡፡ እኛ ከኦሮሞ የተወለድን ስንሆን በክልላችን እየተከናወነ ያለውን ነገር ለአሜሪካ ህዝብና ለታምፓ ነዋሪ ለማሳወቅ እንፈልጋለን›› ብለዋል፡፡

በተቃውሞው ላይ ከነበሩት አንዱ ለዜና አውታሩ ሲናገር ደግሞ ‹‹ለተገደሉት፣ ቤተሰባቸው ለሞተባቸውና በአጠቃላይ እየተሰቃዩ ላሉት ወገኖቻችን ፍትህ እንዲሰጥ ጥሪ እናቀርባለን›› ብሏል፡፡ እነዚህ ሰልፈኞች ይህንን ተቃውሞ ያደረጉ ትላንት የተከበረውን የአሜሪካ የሰራተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡