የደህንነት ጥናት ኢኒስቲትዩት ምሁራን ብሄራዊ መግባባትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ልትማር ይገባታል አሉ፡፡

መረሳ ደሱ እና ዳዊት ዮሀንስ የተባሉት የአይ ኤስ ኤስ ተመራማሪዎች ዛሬ ባቀረቡት ፅሁፍ የዛሬ ሁለት አመት በኢትዮጵያ የተፈጠረው የፖለቲካ ሽግግር በአንዳንድ ክልሎችና በፌዴራል መንግስቱ መካከል ተቀናቃኝነትን እንደፈጠረ በማውሳት ጀምረዋል፡፡ ይህም የፖለቲካ አለመረጋጋትንና ሌሎችንም ግጭቶችን እያስከተለ በመሆኑ ችግሩ ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት መሄዱን ጠቅሰዋል፡፡

ጨምረውም ከዚህ ስር እየሰደደ ከመጣ የፖለቲካና የደህንነት ችግር ለመውጣት ብሄራዊ መግባባት ላይ የሚያደርስ ውይይት ማድረጉ ብቸኛ አማራጭ የመሆኑ ጉዳይ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ፅሁፋቸው ‹‹በኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት ከረጅም ዘመናት አገር ግንባታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል  በአገሪቱ ፖለቲካዊ ታሪክ ላይ ያለው ትርጉም መለያየቱ፣ የማህበራዊ አንድነት እጥረትና በዋና ዋና የአገሪቱ ምልክቶችና ተቋማት ላይ ብሄራዊ መግባባት ላይ አለመድረስ  ቀዳሚዎቹ ናቸው›› ብለዋል፡፡

‹‹ከሌሎቹ አገራት ልምድ እንደታየው የውይይቱ አጀንዳ ራሱ በተሳታፊዎቹ ምክክር ተቀርፆ ከውይይቱ የሚገኘው ውጤትም አስቀድሞ ተቀምጦ መጀመር ይኖርበታል››

በቅርቡ በኢኒስቲትዩቱ የተደረገ አንድ ጥናት ስለብሄራዊ መግባባት በ2008 በኬንያ፣ ከ2014 እስከ 2016 በሱዳን እንዲሁም ከ2017 እስከ 2020 በደቡብ ሱዳን የተደረጉት ውይይቶች ለኢትዮጵያ ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆኑ ማሳየቱን እነዚህ ምሁራን በፅሁፋቸው አውስተዋል፡፡ ይህን መሰሉ ውይይት አሁን ለኢትዮጵያ በአስቸኳይ የሚያስፈልግ እንደሆነ የጠቀሱት ምሁራኑ ውይይቱ ከተካሄደ ቀውስን የሚታደግ ከመሆኑም በላይ ለአገሪቱ የረጅም ጊዜ ለውጥ መሰረት እንደሚጥልም አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከሌሎቹ አገራት ልምድ እንደታየው የውይይቱ አጀንዳ ራሱ በተሳታፊዎቹ ምክክር ተቀርፆ ከውይይቱ የሚገኘው ውጤትም አስቀድሞ ተቀምጦ መጀመር ይኖርበታል›› ያሉት ምሁራኑ፣ በብሄራዊ መግባባት ውይይቱ ላይ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲቪል ሶሳይቲ ቡድኖች መሳተፍ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል፡፡ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን የብሄራዊ መግባባት ውይይቶች ዋና ዋና ተቃዋሚዎችንና ታጣቂዎችን ሳያካትቱ በስልጣን ላይ ባሉት ፕሬዝደንቶች መጀመራቸው የተአማኝነት ጥያቄ ማስነሳቱን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም አስቀድሞ የውይይቱ ውጤት ባለመቀመጡ ውይይቱ እየተንቦረቀቀ ለመግባባትና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስቸግር ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀዋል፡፡ በአንፃሩ የኬንያ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ውይይት በተወሰኑና በተመጠኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮሩ ውጤቱን በቀላሉ ለማግኘት እንደተቻለ አስታውቀዋል፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋናዮችም ይህንን የምስራቅ አፍሪካ ልምድ ተመልክተው የትኛው አካሄድ እንደሚሻላቸው መምረጥ ይችላሉ ብለዋል ምሁራኑ፡፡