“አሜሪካ የኢትዮጵያን ግድብ ለማስቆም የምታደርገው ጥረት ለብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ዘመን ውርስና ቅርስ የሚያስታውስ ነው” – ግሎባል ኢንፎርሜሽን ኔትወርክ

ግሎባል ኢንፎርሜሽን ኔትወርክ ዛሬ ባቀረበው ዘገባ አሜሪካ የኢትዮጵያን ግድብ ለማስቆም የምታደርገው ጥረት ለብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ዘመን ውርስና ቅርስ የሚያስታውስ እንደሆነ አስረድቷል፡፡

Trump, Al sisi and Dr Abiy Ahmed

ሊዛ ቪቭስ የተባለችው ጋዜጠኛ ከኒውዮርክ በፃፈችው በዚህ ዘገባ በፕሬዝደንት ትራምፕ መመሪያ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው እርዳታ ውስጥ 130 ሚሊዮን ዶላር እንዲቆረጥ መወሰኑን አውስታለች፡፡ እንዲቆረጥ የተወሰነው እርዳታ ደግሞ በተለይ ከደህንነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩን አስረድታለች፡፡ ስትዘረዝርም ውሳኔው የደህንነት ድጋፍን፣ የፀረ ሽብር ዘመቻን፣ ወታደራዊ ስልጠናን፣ የፀረ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዘመቻንና የድንበር ጥበቃን የመሳሰሉ ፕሮግራሞች እንዲቋረጡ የሚያደርግ እንደሆነ አስታውቃለች፡፡ በአንፃሩ የሰብአዊ እርዳታዎች ማለትም የምግብ፣ የኤች አይ ቪና የኮቪድ 19 እርዳታዎችን ይህ እገዳ እንደማይመለከተው ጠቅሳለች፡፡

ግድቡ ሲጠናቀቅ ከአፍሪካ ትልቁ የሀይድሮኤሌክትሪክ ፕሮጀክት እንደሚሆን ያስረዳችው ጋዜጠኛዋ በዚህም እስከ 65 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ህይወት እንደሚለወጥ ገልጿለች፡፡ ይህ የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ በኢትዮጵያ የልማት ስትራቴጂ ላይ ጣልቃ እንደመግባት እንደሚቆጠርም ፅፋለች፡፡ በጉዳዩ ላይ ታዋቂውን የኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማንን ያነጋገረች ሲሆን እሱም በሰጠው ማብራሪያ ‹‹ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያን ሉአላዊ ድንበር ጥሶ መግባት ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ታዳጊ አገራት የህዝባቸውን የኑሮ ደረጃ የማሻሻል መብት ላይ የተቃጣም ጥቃት ነው›› ብሏል፡፡

ጋዜጠኛዋ በዘገባዋ ግብፅ በ1959 በብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ወቅት የተፈፀመውን ስምምነት ኢትዮጵያ እንድትቀበል እንደምትፈልግ የገለፀችው ጋዜጠኛዋ አሜሪካም ይህ ስምምነት በዚህ ዘመን እንዲተገበር በማሰብ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እያደረገች በመሆኑን አስረድታለች፡፡