የአንድ የኢትዮጵያ ሲኒ ቡና ዋጋ 50 ፓውንድ (ከሁለት ሺህ ብር በላይ)

የለንደን አንድ ቡና መሸጫ መደብር በዩናይትድ ኪንግደም እጅግ ውድ የሆነውን አንድ ሲኒ ቡና መሸጥ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የዚህ አንድ ሲኒ ቡና ዋጋ 50 ፓውንድ(ከሁለት ሺህ ብር በላይ) ሲሆን ለገበያ የቀረበውም 15 ሲኒ ቡና ብቻ ነው፡፡

ይህ ቡና ቤት ኩዊንስ ኦፍ ሜይፌር የሚባል ሲሆን ይህንን ውድ ቡና አፍልቶ እየሸጠ ያለው ከኢትዮጵያ በጨረታ በገዛው ቡና መሆኑን ገልጿል፡፡ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በሚል በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገው የቡና ቅምሻ ውድድር ላይ አንደኛ የወጣውን ይህንን ቡና አንድ ኪሎውን በሁለት ሺህ ፓውንድ እንደገዛውም አስታውቋል፡፡

ባለፈው ሰኔ ወር በተደረገው ጨረታ የገዘው ይህ ቡና አሁን ለንደን ደርሶ ለደንበኞች ተፈልቶ መቅረቡን ድርጅቱ ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ከድርጅቱ ባለቤቶች አንዷ የሆነችው ቪክቶሪያ ሸፐርድ ስትናገር ‹‹እጅግ ምርጥ የሆነውን ቡና በድርጅታችን ሜኑ ውስጥ ለማካተት በመቻላችን ትልቅ ኩራት ይሰማናል፡፡

እንዲህ አይነት በቀላሉ የማይገኝና ምርጥ ዘር የሆነ ቡናን ለደንበኞቻችን ማቅረብ ምኞታችን ነበር›› ብላለች፡፡ ዘገባው የኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ነው፡፡