“እውነት ከአንባገነኖች ክንድ ትበረታለች”! – የባልደራስ መግለጫ

“እውነት ከአንባገነኖች ክንድ ትበረታለች”! 

የባልደራስ መግለጫ


ብሄራዊ መግባባት ሽብር ባልፈጸመ ሰላማዊ ታጋይ ላይ የሽብር ክስ በመመስረት ህጉን የፖለቲካ ተገዥ በማድረግ አይገኝም!!!እናት አገራችን ውዲቷ ኢትዮጵያ ከአያት ቅድም አያቶች አጥንት ፍላጭ ተማግራ፣ አፈሯ በደማቸው  ተለዉሶ ተቦክቶና ተጋግሮ ለሺዎች ዘመን የቆመች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ነገዶች ባህል ከባህል፣ሃይማኖት ከሃይማኖት ነገድ ከነገድ ተስበጣጥሮ ያቆማት የውህድ ማንነት ተምሳሌት ሀገር ናት፡፡ ይህም በልጆቿ ተጋድሎ ለዘመናት ከውጭ ወራሪ ሀይል ተጠብቃ በመቆየት የጥቁር ህዝብ ፈርጥ እንድትሆን አድርጓታል፡፡

ሆኖም በልጆቿ አጥንትና ደም ራሷን ጠብቃ ብትቆይም በሃሰት የታሪክ ትርክት በገዢዎች መረን የለቀቀ የስልጣን ጥም ውስጣዊ አንድነቷን አስጠብቃ መቀጠል ከፍተኛ ተግዳሮት ሁኖባታል፡፡

የህወሓት/ኢህአዴግ የግብር ልጅ ኦህዴድ/ብልጽግና መራሹ የዚህ ዘመን ተረኛ ገዢ ቡድን በዘመናት መከራና ተድላ ተጋምዶ የነበረውን ወደገደል እያንደረደረ፤ከዚህ ቀደም ከነበረው በባሰ ፍጥነት እየነጎደ እንደሆነ የሰሞኑ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አመራሮች ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበው ‹‹የሽብር ክስ›› እና የፌዴሬሽልን ምክር ቤት ‹‹የትግራይ ክልል ምርጫ››ን አስመልክቶ በነሐሴ 30/2012 የወሰደው አቋም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

ዶ/ር አብይ አህመድ በ2010 ዓ.ም ወደ ሥልጣን በመጡ ሰሞን ‹‹ኢህአዴግ አሸባሪ ነው›› ለዚህም ያለፈውን ይቅርታ በመጠየቅ ለወደፊቱ እንደማይደገም፣ ለበደላቸውም እንደሚክሱ ሲገልጹ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ የሁለት ዓመት የሥልጣን ጉዞአቸው የህዝብ ጥያቄን መፍታት ሲሳናቸው፤ ሌሎች የህዝብን ጥያቄ አደራጅተው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ሲታገሏቸው “ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህ “ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን” ዛቻ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ፣አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም፣ ወ/ት አስካለ ደምሴ እና ሌሎች አባላት ላይ አሻሽለነዋል፣ በሽብር ህግ ስምም ህዝባችንን ስናሸብር ነበር ባሉት አዋጅ መከሰሳቸው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በእጅጉ አሳዝኖታል፡፡

ፓርቲያችን ለውጡ ሀዲዱን መሳቱን በተደጋጋሚ የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳ ቢገልጽም አሁን በመሪዎቻችን ላይ የተዘጋጀው የፈጠራ ክስ “ላም ባልዋለበት…” የሆነ የስርዓቱ ጋሻ ጃግሬዎች በስልጣን ለመቆየት የሚደረግ የተለመደ እኩይ ተግባር እየከወኑ መሆኑ ተጨማሪ ማሳያ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በሌሎች አመራሮቻችን ላይ የተከፈተው የሀሰት ክስ በፍጹም መሪዎቻችንን የማይመጥናቸው ይልቁኑም በፓርቲያችን ውስጥ ባላቸው ጠንካራ ተሳትፎ የሰላማዊ ትግል አርበኝነታቸውን በደንብ ያስመሰከሩ ሰንደቆቻችን ናቸው፡፡ ይህ የኦህዴድ/ብልጽግና የፈጠራ ክስ ማንን ለማሸበር እንደተነሳና በአንጻሩም ከምንም አይነት ህገ-ወጥ ድርጊት እንደማይገታ አስመስክሯል። ይሁንና ይህ አይነት እርምጃ ፓርቲያችን ሲያካሂድ ከቆየው የተጠናከረ ስላማዊ ትግል እንደማይገታው እና ትግሉ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በአጽንዖት ለማስገንዘብ ይፈልጋል፡፡

ኦህዴድ/ብልጽግና ሀገሪቱን በአግባቡ መምራት አቅቶት በቅርቡ ህወሓት በትግራይ ያደረገውን ምርጫ አስመልክቶ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስተላለፈውን አቋም አሳፋሪ ሆኖ አግኝተነዋል። የፌዴሬሽን ም/ቤቱ “ምርጫ እንደተደረገ አይቆጠርም” የሚል አቋም መውስዱ ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለመላው የአገራችን ሕዝቦች ማስገንዘብ ይወዳል፡፡ ምክር ቤቱ በዚህ ውሳኔው ትግራይ በአንባገነኖች ተንኮል ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል እንድትገነጠል የይለፍ ካርድ እንደሰጠ ይቆጠራል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ስህተት የገዢው ፓርቲ አመራሮች በህግም በታሪክም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ የወላይታ ህዝብ “የክልል ልሁን” ጥያቄ ሲያነሳ የዞን አመራሩ “ያልተፈቀደ ስብሰባ” ሊያደርግ ነው ስለሆነም የመከላከያ ሰራዊቱ ማስቆም አለበት በሚል ተልካሻ ምክንያት ከ36 በላይ የንጹሀን ህይወት ተቀጥፏል። የወዳጅነት ፓርክ ምረቃ በሚል ሰበብ “ወታደራዊ ትርዒት” ሲያሳይ የነበረው “ጠንካራ” ሰራዊት ህገ-መንግስቱን አስከብራለሁ የሚል ሰራዊት የትግራይ ህዝብ በጫና ምርጫ አድርግ ሲባልና ህውሓት እንደፈለግሁ እሆናለሁ በማለት ያሻውን ሲያደርግ ይህንን መሳይ እኩይ ተግባር ለማስቆም መቀነቴን ጣልኩ የሚል ምክንያት በማቅረብ በዝምታ ሲያልፈው ተስተውሏል። ከተግባራዊ ወታደራዊ እርምጃ መለስ ምርጫውን ለማስቀረት እና ሕግ ለማስከበር ዲፕሎማሲያዊ ድርድር እና  ጫናን ጨምሮ በርካታ አማራጮች እንደነበሩ ባልደራስ አበክሮ ያምናል፡፡ በዚህ ረገድ ገዢው ፓርቲ ከቃላት ድርደራ በቀር አንዳችም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አለመስተዋሉ የፍላጎት እና የአመራር ብቃት ማነስ እንደሆነ ለመረዳት ከባድ አይሆንም፡፡

የሻሸመኔውንም ሆነ በአካባቢው የነበረውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ “አልታዘዝኩም” በሚል ሹፈት ማለፉንም ልብ ይሏል፡፡ ባልደራስ ለተረኛ ገዢዎች መከላከያ ሠራዊት በከተማ መካከል መብለጭለጭና የገመድ መውጣትና መውረድ “ትርኢቱ”ን አቆይቶ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ገዳዮች እንደ ቱሪስት እየተመላለሱ የዜጎችን ህይወት በማንነታቸው ምክንያት እንደ ቅጠል ሲረግፉ ሃይ ማሰኘት የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር እንደሆነ በአጽንኦት ሊያስገነዝብ ይወዳል፡፡ ይህን የዜጎችን ደህንነት በማንኛውም አካባቢ ማስጠበቅ የፖለቲካ አስተዳደር ሀሁ መሆኑን ለማስታወስም ተገደናል፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤት “እንዳልተደረገ ይቆጠራል” በሚል በቀላሉ ያለፈው ነገር ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ፈይዳ የሌለው በድርድር ሰጥቶ የመቀበል መርህን ያላገናዘበ፣ በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ በሚገኙ የክልል መንግስታት መካከል መጥፎ ልምድን የሚተው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ይህም በስርዓቱ ሆን ተብሎ በሚመስል ቸልተኝነት ሀገሪቱ እየሄደችበት ያለውን መዳረሻው የማይታወቅ የቁልቁለት ጉዞ መጀመሩን ያመለክታል፡፡በመጨረሻም ሀገሪቱን በቅጡ ማስተዳደር ከስልጣን በላይ ማሰብን የሚፈልግ ሁሉንም ህዝብ እና የፖለቲካ ፓርቲ በእኩል አይን ማየትን የሚጠይቅ እንደሆነ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ያምናል። አሁን ኦህዴድ/ብልጽግና እየሄደበት ያለው “አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ” ጉዞ ለሀገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት የማያስገኝ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በዚህ ጥፋትም ለዘመናት ጸጸትና ቁጭት ከማትረፋችንና ዕርስ በርስ ከመወነጃጀላችን አስቀድመን ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባት ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ባልደራስ ይገነዘባል።

ይሁንና ገዥ ፓርቲው ብሄራዊ መግባባት በሚል የጀመረውን ባልደራስን እና ሌሎች የሚመለከታችውን ወገኖች ያገለለ አካሄድ ብሄራዊ መግባባት ያስገኛል ብሎ አያምንም። ሂደቱ ፍሬ እንዲያፈራ ከተፈለገ ተወደደም ተጠላም በህግ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ የሚሆኑበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል። የውይይቶች አጀንዳም በገዥ ፓርቲውና ተቀራራቢ አመለካከት ባላችዉ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ተጻራሪ አመለካከት ባላቸው ፓርቲዎች ጭምር ሊነደፍ ይገባል። ውይይቱም ፍሬ እንዲያፈራ ከተፈለገ በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ በህግ እና ተዛማጅ ሙያዎች ታዋቂነትን ያተረፉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ ያገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች ሊሳተፉበት ይገባል የሚል እምነት አለን።

ገዢው ፓርቲ አገር አክሳሪ የሆነ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማይመጥን ብልጣብልጥነቱን ወደ ጎን በመተው የሚደረጉ ውይይቶችና ድርድሮች ለዘላቂው የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስትነት የሚያስቀጠሉ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የወረስናቸውን ሀሰተኛ እና የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን የሚያቃኑ፣ ህግን በፖለቲካ መሳሪያነት በመጠቀም ህወሓት ሲተገብረው የኖረውን ሰላማዊ ታጋዮችን በሽብር የመክሰስ ልምድ ሊቀር ይገባል ብሎ ፓርቲያችን ያምናል፡፡

በያዝነዉ አዲሱ ዓመት ፓርቲያችን የአሁን እና የመጪውን ትውልድ ህልውና በማስቀጠል የዲሞክራሲያዊ ስርዓት የማዋለድ ጥሪ እያቀረበ ለሂደቱ መሳካትም ጠንክሮ እንደሚሰራ ይገልጻል። ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ሃይሎችና የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ ለብሄራዊ መግባባትና እርቅ እንዲሰሩ በድጋሚ ጥሪያችን እያቀረብን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለመላ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ለአዲሱ ዓመት መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

ድል ለእውነተኛ ለዲሞክራሲ!

መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም

Comments are closed.