የኢዜማ ፓርቲ የቢሾፍቱ ከተማ የአድአ ምርጫ ወረዳ 1 ሊቀመንበር ተገደሉ

በግንቦት ወር መጨረሻና በሰኔ ወር መጀመሪያ ከትግራይ ክልል ውጪ በመላው ኢትዮጵያ ለማካሄድ በታቀደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ 52 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ከነዚህ ፓርቲዎች መካከል ኢዜማ አንዱ ነው።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ጀምሯል። በቢሾፍቱ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ ለመጀመር አንድ ቀን ሲቀረው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የቢሾፍቱ ከተማ የአድአ ምርጫ ወረዳ 1 ሊቀመንበር የነበሩት ግርማ ሞገስ ለገሰ ትላንት እሑድ የካቲት 7 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው ማለፉን ኢዜማ አስታውቋል።

“የኢዜማ አባላት እና አመራሮች ይህን ዜና ስንሰማ ከፍተኛ ሐዘን ተሰምቶናል። ኢዜማ በአባሉ ላይ የተፈፀመውን የግድያ ወንጀል በፅኑ የሚያወግዝ ሲሆን ተጨማሪ መረጃዎችን ሰብስበን እንደጨረስን ዝርዝር ጋዜጣዊ መግለጫ የምንሰጥ መሆኑን እናሳውቃለን።” ያለው ፓርቲው “ለግርማ ሞገስ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እና የትግል አጋሮች ልባዊ መጽናናትን እንመኛለን።” ብሏል።

የኢዜማው አመራር በቢሾፍቱ ከተማ አስደንጋጭ ቢሆንም ማን እንደገደለው እና ለምን እንደተገደለ እስካሁን አልተገለጸም።

ከኢዜማ ጋር በተያያዘ መረጃየኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (አዜማ) የ #ምርጫ2013 የጊዜ ሰሌዳ ላይ በተቀመጠው መሰረት ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢ የሚገኙ የምርጫ ወረዳ መዋቅሮች የምረጡኝ ቅስቀሳ ጀምረዋል።


በአዲስ አበባ የኢዜማ ከፍተኛ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የነፃ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ተሳፋሪዎች ኢዜማን በተመለከተ ያላቸውን ማንኛውንም ጥያቄ እንዲጠይቁ እና ከአመራሮቹ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ የምርጫ ቅስቀሳ ተጀምሯል።
ቅስቀሳው ሊደረግባቸው ከታሰቡ ቦታዎች አንደኛው በሆነው ሽሮሜደዳ አካባቢ «የምርጫ ቅስቃሳ ስለመጀመሩ አናውቅም» ባሉ የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ቅስቀሳው ሳይደረግ ተስተጓጉሏል።
ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ጥያቄዎችን ሲመልሱ የነበሩት የኢዜማ መሪዎች ተሳፋሪዎቹን ኢዜማ ቅዳሜ የካቲት 13 ቀን 2013 ዓ.ም የሚያደርገው የምርጫ ቅስቀሳ ይፋዊ ማስጀመሪያ ክንውን ላይ እንዲገኙ ግብዣ አድርገውላቸዋል።