የደቡብ ዕዝ ትክክለኛውን የዳዊት አብርሃ ፎቶ እንዲለጥፍ ተጠየቀ – ሃጎስ ሰልጠነ ፍስሃዬ ብሎ የለጠፈው ሰው ስም በቀለ ሻንቆ ባልቻ ነው

የደቡብ ዕዝ ባለፈው ሳምንት “የመከላከያ ሰራዊቱንና የጦር አመራሮችን ስም በማጠልሸት የአገርን አንድነት አደጋ ውስጥ የሚጥል የጥላቻና የሃሰት መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ያሰራጭ የነበረው ግለሰብ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ለመውጣት ሲሞክር በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ሌሎች ከአገር ሊወጡ የነበሩና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች ጭምር መያዛቸውን ኦፕሬሽኑን የመሩት ሌ/ኮ ግርማ አየለ አረጋግጠዋል::” ሲል ያሰራጨው ግለሰብ ፎቶ ትክክለኛ እንዳልሆነ ቤተሰብ እና ልጁን የሚያውቁት የዝዋይ አካባቢ ተወላሆች ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።

‘ የጦር ሃይሎች ም/ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሌ/ጄ አበባው ታደሰን ጨምሮ ፣ ጄኔራል መኮንኖችንና ከፍተኛ የጦር አዛዦች በትግራይ ልዩ ሃይል ተገድለዋል’ የሚልና ሌሎችንም የሀሰት መረጃ “የትግራይ ልዩ ሃይል ድል” በሚል ፍሪደም ቲቪ በተባለ የዩቲዩብ አድራሻ በተለያ ጊዜ ያልተጨበጠ መረጃ ያሰራጭ የነበረው ሃጎስ ሰልጠነ ፍስሃዬ የተባለው ግለሰብ ከአዲስ አበባ በመነሳት ኬንያ ከዛም ወደ ዩጋንዳ ካምፓላ ለመውጣት ሲሞክር ነው ሃዋሳ ላይ በደቡብ ዕዝ የሰራዊት አባላት በቁጥጥር ስር የዋለው: 

ስራውን እንዲሰራ የቀጠረው እንግሊዝ አገር የሚኖረው ዳዊት አብርሃ ዘረዝጊ የተባለ ሰው መሆኑንና ለአገልግሎቱም 6 መቶ የአሜሪካን ዶላር ይከፍለው እነደነበር ገለሰቡ ተናግሯል::

የሚያሰራጨውን የሃሰት መረጃም እንግሊዝ አገር ሆኖ ዩቲዩቡን ከሚያስተዳድረው ዳዊት አብርሃ እንደሚሰጠውና እሱም በውጭ ካሉ አፍራሽ እንቅስቃሴ ካላቸው ከተለያዩ የቴሌቪዝን ጣቢያዎችና ከግለሰቦች ማህበራዊ ገፅ የሚያገኘውን ያልተጣራ መረጃ አሰሪውን በማስፈቀድ ይጠቀም እንደነበርም በተለይ ለደቡብ ዕዝ ሚዲያ ቡድን ተናግሯል:

ይህንን ስራ ከአመት በፊት እንደ ጀመረ የሚናገረው ግለሰቡ፣ መንግስት በትግራይ የህግ ማስከበር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ያልተጨበጠ የበሬ ወለደ መረጃ ማሰራጨት እንደጀመረና “እየቆየሁ ስሄድም እየሰራሁት ያለው ወንጀል የደህንነት ስጋት ላይ ስለጣለኝ፣ ከአገር ለመውጣት ስንቀሳቀስ ነው በመከላከያ በቁጥጥር ስር የዋልኩት” ሲል መግለጹ የሚታወቅ ነው።

ደቡብ ዕዝ የሃሰት መረጃ አሰራጭውን ሃጎስ ሰልጠነን ጨምሮ ከአገር ሊወጡ የነበሩ  8 ሰዎችን እና 4 በህገ ወጥ ዝውውሩ ላይ ተሳትፎ የነበራቸውን ለፌዴራል ፖሊስ ማስረከቡን ሌ/ኮ ግርማ አረጋግጠዋል ፡፡

የደቡብ ዕዝ ዜናውን ሲያሰራጭ ዋና ተጠርጣሪውን  ሃጎስ ሰልጠነ ፍስሃዬ ብሎ ፎቶ የለጠፈው የበቀለ ሻንቆ ባልቻ ነው የሚሉት አቤቱታቸውን ያቀረቡት ወገኖች በርግጥ በቀለ ሻንቆ በ እስር ላይ ቢገኝም እንዲህ ዓይነቱን ሥራ የሚፈጽም አይደለም፤ የገንዘብ አቅም እንኳን የሌለው በውጭ ሃገር ባሉ ጓደኞቹ አንዳንድ ጊዜ እርዳታ እየተደረገለት የሚኖር ነው ብለዋል።

በርግጥ አንድ ፎቶ ቤት ያለው ሰው እንግዶችን መንገድ አሳይ ብሎ የሚኖርበትን የችግር ሕይወት በመጠቀም መንገድ እንዲያሳይ ልኮታል። ከተያዙት ሰዎች መካከልም እርሱ አለበት ግን በቀለ ሻንቆ እንዲህ ባለው ነገር ላይ ተሳታፊ ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል። የደቡብ እዝም ዋናውን ሃጎስ ሰልጠነ ፎቶ በሚመስል መልኩ የበቀለ ሻንቆን ፎቶ መለጠፉ ከበስተጀርባው ሌላ ነገር ሊኖረው እንደሚችል ገምተናል ስለዚህ መከላከያው እንደገና እንዲመረምር ጥሪያችንን እናቀርባለን ሲሉ ተናግረዋል።