ልክ የዛሬ ወር ሁለት የጁንታው ከፍተኛ አመራሮች እጃቸውን መስጠታቸውን የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት

ልክ የዛሬ ወር ሁለት የጁንታው ከፍተኛ አመራሮች እጃቸውን መስጠታቸውን የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሀመድ ተሰማ አረጋገጡ።  ለመከላከያ ሠራዊታችን እና ለፌዴራል ፖሊስ እጃቸውን የሰጡት ሜጀር ጄኔራል መሀመድኢሻ ዘይኑ እና ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ በርሄ ናቸው ብለው ነበር።

ወንጀላቸውን ሲዘረዝሩም ሜጀር ጄኔራል መሀመድ ኢሻ ዘይኑ ቀደም ብሎ የምዕራብ ዕዝ ም/አዛዥ ለኦፕሬሽን የነበረ፣ ከዚያም በዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ በጡረታ በክብር ተሰናብቷል። በኋላም ጁንታውን ተቀላቅሎ ኃይሉን ሲመራና ሲያዋጋ ቆይቷል፡፡ መቀሌ ሲያዝም ወደ ጫካ ሸሽቶ አሁን በተደረገው አሰሳ በሰላማዊ መንገድ እጁን ለሠራዊታችን ሰጥቷል ፡፡

ብ/ጄኔራል ሙሉጌታ በርሄም በምስራቅ እዝ፣ የዕዙ ኮማንድ ሆኖ ሲሰራ በጡረታ ቢገለልም፣ መቀሌ በመሄድ ከጁንታው ጋር ተቀላቅሎ እስከ መጨረሻው ድረስ አመራር ሲሰጥ ቆይቶ አሁን እጁን ለሠራዊታችን ሰጥቷል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ህወሃት ጥቃት በፈጸመበት ወቅት “ዋና አስተባባሪ ነበሩ” ተብሎ የተገለጸላቸው እነዚህ ሁለት ጀነራሎች ዛሬ ከእስር የመለቀቃቸው ዜና አነጋጋሪ ሆኗል። 

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተጠርጣሪዎቹ ፈጸሙ በተባሉበት ወንጀል ምርመራ ሲካሄድባቸው የቆዩ ቢሆኑም የምርመራ ቡድኑ ባደረገው ማጣራት የወንጀል ተሳትፎአቸው ዝቅተኛ መሆኑን በመገንዘብ ምርመራው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን ቢሮው ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ህወሃት ጥቃት በፈጸመበት ወቅት “ዋና አስተባባሪ ነበሩ” ብሎ የገለጸላቸውና እጃቸውን ሰጥተው በቁጥጥር ስር የሚገኙ አራት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን የወንጀል ምርመራ ማቋረጡና አስታውቆ ከእስር እንዲለቀቁ የተደረጉት የጦር መኮንኖች፦

1. ሜ/ጀ መሀመድ ኢሻ ዘይኑ ትኩእ

2. ብ/ጀ ሙሉጌታ በርሄ ይልማ

3. ኮ/ል ገ/እግዚአብሔር ገ/ሚካኤል እና

4. ኮ/ል ገ/ዋህድ ኃይሉ መሸሻ ናቸው፡፡

መከላከያው እነዚህ 4 የጦር መኮንኖች እጃቸውን መስጠታቸውን ቢገልጽም ፖሊስ ዛሬ ሲናገር ግን 

በጥቅምት 24 በሰሜን ዕዝ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩት መኮንኖቹ የመከላከያ ሰራዊት ባደረገው ክትትል ተይዘው ለምርመራ ቡድኑ ተላልፈው የተሰጡ  ናቸው ብሏል።