የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጽሁፍ መል ዕክት አስተላለፉ

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጽሁፍ መል ዕክት አስተላለፉ። ተመስገን በጽሁፋቸው “የቀሩት የስግብግብ ጁንታ አመራሮች ነፍስም እንደ ወፏ ሁሉ በእጃችን መዳፍ ውስጥ መሆኑን እኛ እንደ እናት እናውቀዋለን” አሉ። የተመስገንን ውስጠ ወይራ አጭር የጽሁፍ መልክት እንደወረደ እናቀርበዋለን።

“ራስ ሳይጠና ጉተና”

“የማያድግ ልጅ ከእናቱ ጀርባ ላይ ታዝሎ ያፉጫጫል”

ከላይ የተጠቀሱት አባባሎች የአበው ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ናቸው። ራስ ሳይጠና ጉተና ማለት ራስን መሸከም በማያስችል ሁኔታ ሌሎች ግዝልዛል ጌጣጌጦች በአናት ላይ ደራርቦ ለመሸከም  መሞከር ለራስ ህልውና አደገኛ መሆኑን አመላካች ነው። ቅድሚያ የራስን ደህንነት፣ ህልውና፣ የመኖር ዋስትና ሳያረጋግጡ ሌሎች ድሪቶዎችን መከማመር የመኖር ተስፋን እንደማጨለም ይቆጠራል እንደማለት ነው።  አንዳንዴ ገደል አፋፍ ላይ ቆሞ ትልቅ ቋጥኝ ከቆምንበት የገደል አፋፍ በላይ ከፍታ ነጥብ ላይ ሆኖ ቋጥኙን ለማንከባለል የሚታገልን አካል እንደ መርዳት ይቆጠራል። የምንረዳው ራሳችንን ለመጥፋት ነው ማለት ነው። እኛ ገደል አፋፍ ላይ ቆመን ትልቁ ቋጥኝ ተንከባሎ እኛንው ወደ ገደል ገፍቶ እንዲያንኮታኩተን ሌት ተቀን መስራት ማለት ነው።

ሁለተኛው አባባል በእግሩ መሄድ የማይችል፣ መሄድ ቢችልም ብዙ እርቀት የማይጓዝ ህፃን በእናቱ ጀርባ ላይ መታዘሉ ግድ ነው። ይሁን እንጅ ታዝሎም የእናቱን ጆሮ የሚያደነቁር ፉጨት መልቀቅ ብቻ ሳይሆን ፋጨቱ ከጨቅላው ህፃን በላይ ሲሆን አስገራሚ ነው። እናቱ እሩህሩህ የእናትነት አንጀት፣ አዝሎ የማሳደግ የተፈጥሮ ግዴታ፣ እስከ ዘጠኝ ወር በውስጥ አቅፎና ተንከባክቦ ራስን የመተካት አስገራሚ የፍጡራን ተግባራዊ ትዕይንት እና ሌሎችም ምክንያቶች የአስገራሚ ልጇን ፉጨት ተቋቁማ ለማሳደግ ጥረቷን አታቋርጥም። እናት በልጇ ድርጊት አንጀቷ እጥፍ፣ ቆሽቷ እርር እና ጨጓረዋ ቅጥል ቢልም ሀዘኗ ቢኖርም ለልጇ ክፉ አትመኝም። ባይሆን እርር ብላም ልቦና ስጠው ልትል ትችላለች። ሆኖም ሌላው ተመልካች የልጁን እናቱ ጀርባ ላይ ሆኖ ማፏጨት የሚያዬው እንደ እናት በትዕግስትና በኃዘኔታ ሳይሆን ይሄ ባለጌ፣ ድኩማን፣ ባጭር ይቅጭህ በሚል መንፈስ ነው። 

ትህነግ ከላይ የተገለፁ አባባሎች ተግባራዊ ምሳሌ ነው። የሚገርመው ደግሞ ሁሌም ከስህተቱ የማይማር፣ የማይፀፀት፣ በስህተት ላይ ስህተትን የሚደራርብ ጉድ መሆኑ ነው። ከወደቁ በላይ መንፈራገጥ ትርፉ መላላጥ ነው። ፈላስፋና አዋቂውን አባት ሊገዳደሩ የሞከሩ ግብዞች አንዲትን ወፍ በእጃቸው መዳፍ ውስጥ አስገብተው ይህች ወፍ በህይወት አለች ወይስ ሞታለች? አዋቂ ከሆኑ እስኪ ይንገሩን? ይበሉ? ብለው እንደፈተኗቸው ሁሉ። ፈላስፋው እና አዋቂው ሰውም የወፏ የህይወት ህልውና በእጃችሁ ነው፤ ከፈለጋችሁ ጨፍልቃችሁ መግደል፣ ስትፈልጉም እፉኛችሁን ከፍታችሁ ህይወቷን ማዳን ትችላላችሁ እንዳሉት ሁሉ። የቀሩት የስግብግብ ጁንታ አመራሮች ነፍስም እንደ ወፏ ሁሉ በእጃችን መዳፍ ውስጥ መሆኑን እኛ እንደ እናት እናውቀዋለን። አንዳንዶች እንደ ቴፕ ሪከርደር የገባላቸውን ካሴት የሚያጫውቱ በመሆናቸው ምክንያት፣ አንዳንዶችም በለዘብተኛ አቋማቸው ከመሞት መሰንበት ስለሚሻል በነፍስ ብንይዛቸው ይሻላል በሚል መታገሳችንን ልቦናቸው እያወቀ በደሀው ህዝብ የመኖር ዋስትና ላይ አደገኛ ቁማር መጫወት  ጀመሩ። ጭራሽ የካቲት ፩፩ መቀሌ እናከብራለን ብለው ሞኞችን ለማሞኘት  ሞከሩ። ይገርማል። 

ይህ አንሶ በእኛው አባይ ፖለቲካ የተጠመዱ ግብዞች መሾፈር የጀመሩ፣ የአባቶቻችንን ብቻ ሳይሆን የእኛን ክንድም የቀመሱ፣ በለውጥ መሪያችን ድጋፍና ጥረት ከአሸባሪነታቸው ችንካር የተላቀቁ፣ በውስጥ ያልተሳካላቸው፣ በውጭም በሀገራችን ድጋፍ የአይን ጉድፋቸው የተጠረገላቸው ጉዶች፣ ኢትዮጵያ እንኳንስ ለቅርብ ዘራፊና ሙሰኛ መሪዎች ይቅርና ለውጭ ወራሪዎችም እጅ ያልሰጠች፣ ያልተንበረከከች፣ የራሷን ብቻ ሳይሆን አቅም ሳይኖራቸው እና እንደ ወፏ መዳፋችን ውስጥ የሚገኙ ተላላኪዎች ለእነሱ ነፃነት መረጋገጥ ፋና ወጊ ሚና የተጫወተች ሀገራችን መሆኗን የሩቅም የቅርብን ታሪካችን ይመሰክራል። የሚገርመው ደግሞ ማንም ቢመጣ አንንበረከክም፣ አንሸነፍም፣ እኛ ለውጊያ የተፈጠርን ነን የሚለው የታራክ ዝቃጩ ከፋፋይ ስግብግብ ጁንታ በራሱ መሬት፣ ዕቅድና ፍላጎት አከርካሪው ሲሰበር ከቅጥረኛ፣ ሙሰኛና ተላላኪ ጎረቤቶች ጋር ተሰልፎ ዕድሉን ለመሞከር ሽር ጉድ ማለቱ ሌላ የታሪክ ጥቁር ነጥብ እና ጠባሳ ከማስቀመጥ ሌላ የሚያተርፈው ነገር እንደሌለ ልቦናው ያውቀዋል።

ሁሉንም በንቃት እየተከታተልን ነው። ጥንቃቄያችን እና ትዕግስታችን ለንፁሀን ዜጎች ነው። ቀይ መስመሩ ታልፎም የምንታገሰው ከፍርሀትና አቅም እጦት ሳይሆን ለንፁሀን ህዝቦች ካለን ክብር ብቻ ነው። አልያማ እኛ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያውያን ልጆች ነን። መቼ መነሳት እንዳለብን እናውቃለን። ከተነሳን ደግሞ በነቋሪዎች ፍላጎትና ዕቅድ ሳይሆን በራሳችን ነው። ማንም እኛ ዓቅደን የምንሰራውን፣ የእኛ ሀብት የሆነውን ሁሉ የመከልከልና የመዝረፍ ተፈጥሯዊም ህጋዊም ዓቅምም ይሁን ስልጣን እንደሌለው ያውቃል። እናም ነቋሪ ሙሰኛና ዘራፊ የጎረቤቶቻችን መሪዎች ከሌሎችና ከራሳቸው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ኮትኩተው ካሳደጉት ስግብግብ ጁንታ አሳፋሪ ታሪክ፣ ስግብግብ ጁንታውም በተመሳሳይ ከውድቀቱ መማር ይገባቸዋል። ካልሆነ እንደለመዱት ከመከራቸው እንዲማሩ ይገደዳሉ። ሁሉ ነገር ለእኛ የእምቧይ ካብ ነው። ይሄው የካቲት ፩፩ በመቀሌ ሳይሆን ገደል ውስጥ ተወሽቀው አሳለፉት። ነገ ደግሞ ልቦና ካልገዙና ከስህተታቸው መማር ካልቻሉ የተወሸቁበት ገደል ውስጥ ይቀበራሉ። ምርጫው ግን በእጃቸው ነው።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!