ሕወሓት ትግራይን ሶማሊያ ለማድረግ እየሰራ መሆኑ በድርጊቱ እየተጋለጠ መሆኑ ተነገረ

ሕወሃት የፈንቅል አመራር የማነን ጨምሮ ለትግራይ ሕዝብ እርዳታ እያከፋፈሉ የነበሩ ዜጎችን እየገደለ ሲሆን ባለፈው ሳምንትም 2 እርዳታ የጫኑ የከባድ መኪና ሹፌሮችን መግደሉን መዘገባችን ይታወሳል። በየስፍራው ራሱን ደብቆ የሚገኘው ይኸው የሕወሓት ኃይል በትግራይ የመብራት መስምሮችን በመቁረጥ በአሁኑ ሰዓት ሕዝቡ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መብራት የለውም። 

ዛሬ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሆኑ ወጣቶችን ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ እያለ ከመቀሌ እንደወጡ የህወሃት ታጣቂዎች ተኩስ በመክፈት ተማሪዎቹን የማገት ሙከራ አድርገዋል። ወዲያውኑ የመከላከያ ሰራዊቱ ደርሶ የሕወሓት ታጣቂዎችን በመደምሰስ ተማሪዎቹን ለማትረፍ እንደተቻለ ተኩስ ተከፍቶባቸው ከተረፉት ተማሪዎች መካከል አንዱ ለዘ-ሐበሻ ዘጋቢ ነግሮታል። ከቀናት በፊት የህወሓት ታጣቂዎች በአውቶቡስ ላይ በፈጸሙት ጥቃት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መግደሉን ተከትሎ በስጋት ትግራይን እየለቀቁ የሚገኙት የሌሎች ብሔር ተወላጆች ሕወሓት ትግራይን ወደ ሶማሊያነት እንድትቀየር እየሰራ ነው። በአሁኑ ሰዓት ትግራይ ሶማሊያ ሆናለች ሊባልም ይችላል ያለው ተማሪው ሕዝቡ ካልነቃና ከመንግስት ጋር ካልተባበረ ሕወሓት ያቺን ምድር ሶማሊያ ማድረጉን ይቀጥላል ይላል።