‹‹ኤክሳይል ፓተርን›› የተሰኘው የፎቶ ቅንብር ኤግዚቢሽን ሴኡል በሚገኘው ኧርባን ፕሉቶ ጋለሪ ለአንድ ሳምንት ሲከናወን ቆይቶ ተጠናቋል፡

‹‹ኤክሳይል ፓተርን›› የተሰኘው የፎቶ ቅንብር ኤግዚቢሽን ሴኡል በሚገኘው ኧርባን ፕሉቶ ጋለሪ ለአንድ ሳምንት ሲከናወን ቆይቶ ተጠናቋል፡፡

የስራዎቹን ስብስብ በኤግዚቢሽን መልክ ያቀረበው በረከት አለማየሁ ይባላል፡፡ በረከት ኢትዮጵያዊ ሲሆን ወደደቡብ ኮሪያ የገባው እ.ኤ.አ በ2014 ነበር፡፡ አሁን በሴኡል ነዋሪ ነው፡፡ በኤግዚቢሽኑ ላይ ያቀረባቸው ስራዎች ከ2016 እስከ 2018 ባለው የክረምት ወቅት በደቡብ ኮሪያ ከተሞች ያነሳቸው ፎቶግራፎች ናቸው፡፡ በረከት ሲናገር ‹‹በሞቃት አገር የተወለድኩ የውጭ አገር ዜጋ እንደመሆኔ በ2014 እዚህ ስገባ በክረምቱ አየር ፀባይ ክፉኛ ተጎዳሁ፡፡ በተለይ ከ2016 እስከ 18 ባለው ጊዜ በህይወቴ ገጥሞኝ የማያውቅ አስገራሚ ልምድ አሳልፌያለሁ፡፡ የክረምቱ ወራቶች በጠጣር በረዶ ብቻም ሳይሆን በሚያምሩ ቀለማትም የተሞሉ ናቸው፡፡ ክረምቱ የራሱ የሆነ ቅርፅ፣ አነባበር፣ ብርሀንና ስበት ያለው ነው›› ብሏል፡፡ በእነዚያ ወቅቶች ያየውን ሁሉ በፎቶግራፍ ቀርፆ እንዳስቀመጠ አስረድቶም ፎቶዎቹን በመቆራረጥ ሌላ አዲስ ምስሎችን ለመፍጠርና ለእይታ ለማብቃት መቻሉን ጨምሮ ገልጿል፡፡ በረከት የሚውዚክ ሜይ ዴይ ኢትዮጵያ አባል በመሆን ወደኮሪያ ለመሄድ የቻለ ነው፡፡ አሁን የፎቶ ፓተርን ባለሙያ፣ ማህበራዊ አንቂና ፀሀፊ ሆኖ በዚያው ይኖራል፡፡