የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከ4 ቀን በኋላ ዝምታውን ሰበረ | ለጌታቸው ረዳ እና ከገብረገብረጻድቅ ምላሽ ሰጠ

Colonel Getenet Adane

ራሱን የህወሓት ጦር ቃል አቀባይ ነኝ ብሎ የሚጠራው ገብረ ገብረጻድቅ በ”ኦፕሬሽን አሉላ አባነጋ” ሁለት የኢትዮጵያ ክፍለ ጠሮች ሙሉ ለሙሉ፣ አራት ክፍለጦሮች በከፊል ተደምስሰዋል፤ በርካታ የኤርትራ ብርጌዶችም ክፉኛ ተመተዋል ሲል በትግርኛ ቋንቋ በሰጠው መግለጫ አስታወቀ።

“በዚሁ ከዓርብ ጀምሮ እስከዛሬ በቀጠለው ጠላትን የመቅበር ዘመቻ ጠላት ግብአቱ-መሬቱ እየተፈፀመ ነው።” ያለው ገብረገብረጻድቃን “- የ11ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮ/ል ሐሴን በትግራይ ሰራዊት እጅ ይገኛል፤ የበርካታ ክፍለጦሮችና ብርጌዶች አዛዦች ተገድለዋል” ሲል ገልጿል።

“በአሁኑ ሰዐት ከ1300 በላይ የሆኑ ወታደሮች በትግራይ ሰራዊት ምርኮ ስር ይገኛሉ፣” ያለው ገብረገብረጻድቅ 11ኛ፣ 20ኛ፣ 21ኛ፣ 24ኛ፣ 25ኛ፣ 31ኛ እና 32ኛ ክፍለ ጦሮች ከተወሰኑ የኤርትራ ክፍለ ጦሮች ጋር በመሆን በጠላት ወገን የተሰለፉ ሲሆን ከነዚህ 11ኛ እና 31ኛ ክፍለ ጦሮች ሙሉ በሙሉ ሲደመሰዱ ሌሎች ደግሞ በግማሽና ከዛ በላይ በሆነ መጠን ተሽመድምደዋል።” ሲል በመግለጫው ጠቅሶ እስካሁንም
-14 መድፎች፣
– 13 ሞርታሮች፣
– 60 መገናኛ ሬድዮኖች፣
– 80 መኪኖች ፣
– ስፍር ቁጥር የሌለው ጥይት በሕወሓት መማረካቸውን በሰጠው መግለጫ ላይ አብራርቷል።
ገብረ ይህን ይበል እንጂ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከአራት ቀን በኋላ ለሕወሓት መረጃዎች ምላሽ ሰጥቷል።

” የአሸባሪው ህወሀት ቡድን ርዝራዦች ፤ ድል ሲርባቸው ፣ ውሸትን ማጥገብ ስራዬ ብለው ተያይዘውታል ” ሲሉ የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ኮ/ል ጌትነት አዳነ አስታወቁ ፡፡
አሸባሪው ህወሀት ከመሰሎቹና ተባባሪዎቹ ከሆኑ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመሆን ሃገራዊ ምርጫውን ፣ የህዳሴ ግድባችንን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ለማደናቀፍ እና “አለሁ” ለማለት የተለያዩ ትንኮሳዎችንና የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሰሞኑን ከፍቶ እንደነበር ይታወቃል።
ኮሎኔል ጌትነት እንዳሉት ፣ በቆላ ተንቤን እየተሹለከለከ እሱ እንደ ልማዱ ተደብቆ ፣ በቅርበት የማይመራውን ውጊያ ፣ ሚሊሻ እንዲሁም ምንም ወታደራዊም ሆነ የአስተሳሰብ ብስለት የሌላቸውን ወጣቶች እሳት ሲማግድ ቋይቷል።
የአሸባሪው ህውሀት ቅሪትና ጥቂት መሪዎች ለህግ ካልቀረቡ ይህ አይነት ማታለል ስለማያቋርጥ ፣ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን መሪዎችን አድኖ የመያዝ ኦፕሬሽኑን በስፋት እያከናወነ ይገኛል።
እስካሁን የተገኘውን ውጤትም በቅርብ ከሚመዘገቡ ተጨማሪ ድሎች ጋር ደምረን ይፋ እናደርጋለን ብለዋል ።

እነሱ ምርጫ ለማደናቀፍ ቢሞክሩም ኢትዮጵያዊ መርጣለች። አባይ እንዳይሞላ ቢሰሩም በቅርቡ ሞልተን እናሳያቸዋለን ያሉት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ፣ ያሰቡትን ማድረግ ቢችሉ ኑሮ የዓለም መንግስታት እነሆ አለን አደራድሩን ለማለት እንጂ ፤ ድል አድርገን ሃገር እንመራለን የሚለው ለማታለያ ለጊዜው ይጠቀሙበት እንጂ ፣ እንደማይሆን አሳምረው እነሱም ያውቁታል ብለዋል።
በቅርቡ ደግሞ ጀ/ል ብርሃኑ ጥላሁንን አፍነናል ፣ ኮ/ል ሻምበል በየነን /ባለ ከዘራውን/ ገለናል ይሉናል። ይህም የትግራይን ህዝብ ለማታለል እና ተስፋ እንዳይቆርጥ መሆኑ ግልጽ ነው ፡፡ እኒህ ወሬያቸው ፣ ምኞታቸው እና ተግባራቸውም ሽብር ስለሆነ በውጊያ ያጡትንና የተራቡትን ድል ፤ በወሬ ሊያገኙ ሲመኙ ውሸታችሁን ጠገብን ልንላቸው ይገባል።
“ነብስ ካለ መንቀሳቀስ አይቀርም” እንዲሉ እስትንፋሳቸው ከውጊያ ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነው ፡፡ እኛ ደግሞ በተግባር የሽብር መሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ህግ እንደምናስከብር እርግጠኞች ነን። ውጤቱንም ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ፡፡

ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ