በሳዑዲዓረቢያ ወረቀት ያላቸውም፤ የሌላቸውም ኢትዮጵያዊያን እየታፈሱ ነው

የሳኡዲ አረቢያ ፖሊስ ባለፉት አስር ቀናት ባደረገው ዘመቻ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ማሰሩን ሚድል ኢስት ሞኒተር ዛሬ ዘግቧል፡፡ ጁን 11 ቀን በተጀመረው በዚህ ዘመቻ ዶክመንት ያላቸውም ሆኑ ዶክመንት የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን እንደሚታፈሱም ገልጿል፡፡
በሳኡዲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለጋዜጣው ለጋዜጣው እንደገለፁት ኢትዮጵያዊያኑ የደንብ ልብስ ባለሰቡ ፖሊሶች ከመንገድ ላይና በለሊት ከቤታቸውም እየተወሰዱ ይገኛሉ፡፡ አንድ በጅዳ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሲናገር ‹‹ፖሊሶች ማንኛውንም ሀበሻ እንድናፍስ ታዘናል እያሉን ነው፡፡ ምክንያቱን አይነግሩንም፡፡ መንገድ ላይም ኢትዮጵያዊ የሚመስል ሰው ካዩ ያስቆሙታል›› ብሏል፡፡
‹‹በሳኡዲ አረቢያ በስደተኞች ላይ የእስር ዘመቻ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም›› ያለው ጋዜጣው በዚህ ዶክመንት በሌላቸው ስደተኞች ላይ በሚደረገው ዘመቻ የመጀመሪያ ተጠቂ የሚሆኑት በአገሪቱ ቁጥራቸው የበዛው ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ አውስቷል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2013 በተከናወነው ዘመቻ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከመታሰራቸውም በላይ ወደመቶ ሺህ ያህሉ ደግሞ ወደአገራቸው እንዲመለሱ ተደርጎ እንደነበር ጨምሮ ጠቁሟል፡፡
ይሁን እንጂ የሰሞኑን ዘመቻ ከበፊቶቹ ለየት የሚያደርገው ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ያላቸውም እየታሰሩ መሆኑ ነው ብሏል ዘገባው፡፡
ጀይላን ኢትዮጵያዊ ቢሆንም የተወለደው ግን በሪያድ ነው፡፡ ይሁንና ባለፈው ሳምንት ከአንድ ካፌ ውስጥ ተይዞ ጁን 12 እና 13 በሳኡዲ ዋና ከተማ ታፍሶ እስር ቤት ለማሳለፍ ተገዷል፡፡ ለጋዜጣው ሲናገር ‹‹ፖሊሶች መጥተው የነበርንበትን ጠረንጴዛ ከበቡት፡፡ ይህን ጊዜ አብረውኝ የነበሩት አመለጡ፡፡ እኔ ግን የምኖረው በህጋዊ መንገድ እንደሆነና አስፈላጊዎቹ ወረቀቶች በሙሉ እንዳሉኝ ላስረዳቸው ብሞክርም ሊሰሙኝ አልፈለጉም፡፡ ሻይ እየጠጣሁ ጋዜጣ አነብ የነበርኩት ሰውም በአንዴ እጄ ላይ ሰንሰለት የታሰረልኝ ሆንኩኝ›› ብሏል፡፡
ጀይላን እንዳለው ከእስር እንዲፈታ ያስደረገው ሳኡዲ አረቢያዊ ቀጣሪው ነበር፡፡ ይህኛው ዙር የእስር ዘመቻ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ከመዲና ስድስት መቶ እንዲሁም ከጂዛን ዘጠና አራት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ማስለቀቃቸውን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጋዜጣው እንዳለው ከዚያ በኋላ ሌሎች በርካቶች ታስረዋል፡፡
በጅዳ የሚገኙት የኢትዮጵያ ምክትል ቆንሲላ ጄኔራል ነብዩ ተድላ ለጋዜጣው ሲናገሩ ‹‹እስሩ እየተፈፀመ ያለው ከዋና ዋና ከተሞች በተጨማሪ በገጠር አካባቢዎችም ጭምር በመሆኑ ምን ያህል ሰው እንደታሰረ ለማወቅ አልቻልንም፡፡ ይሁንና የማስፈታት ጥረታችንን እንቀጥላለን›› ብለዋል፡፡ በጂዛን እስር ቤት የሚገኘውና በድብቅ እስር ቤቱ ውስጥ በገባ ስልክ ለጋዜጣው ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገው ደሱ ሲናገር ደግሞ ‹‹በጂዛን በአንድ ክፍል ውስጥ የታሰርነው ከሰማኒያ እስከ ዘጠና ነበርን፡፡ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ግን ይህ ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል፡፡›› በማለት አስረድቷል፡፡ ቢያንስ ሶስት ኢትዮጵያዊያን የሳኡዲ ፖሊሶች ቤታቸውን ሰብረውና ንብረቶቻቸውን ወስደው እንዳሰሯቸው ለጋዜጣው ገልፀዋል፡፡
በተለይም በጅዳ የሚገኘውና በርካታ ኢትጵያዊያን የሚኖሩበት ኪሎ ተማኒያ ዋነኛው የዘመቻው አካል ነበር፡፡ መሀመድ የተባለው ኢትዮጵያዊ በዚህ ሰፈር ከሶስት ሌሎች የአገሩ ዜጎች ጋር በደባልነት ከሚኖርበት ቤት አካባቢ እያለ ፖሊሶች ቤቱን ሰብረው ሲገቡ ተመልክቷል፡፡
በወቅቱ የነበረውን ሲያስረዳም ‹‹ፖሊሶቹ ልክ እንደገቡ ሀበሻ ሀበሻ እያሉ ደባሎቼን ማሰር ጀመሩ፡፡ አንደኛው ደባሌ እያለቀሱ በነበሩት ሚስቱና ልጁ ፊት በሰንሰለት ታሰረ፡፡ ከዚያም ይዘውት ሄዱ›› ብሏል፡፡ ጃፋር የተባለው ኢትዮጵያዊ ዶክመንት ያለው መሆኑን የተናገረ ሲሆን ጁን 15 በዚሁ ሰፈር የነበረውን ዘመቻ በቪዲዮ ቀርፆ ለጋዜጣው ሰጥቷል፡፡ በቪዲዮው ላይ ፖሊሶች ቤቱ ገብተው የኮመዲኖውን ሲበረብሩና እቃ ሲወስዱ ይታያል፡፡
በወቅቱ ሞባይል ስልኩንና አንድ ሺህ ስድስት መቶ ሪያል እንደወሰዱበት የሚናገረው ጃፋር በቪዲዮ ባስተላለፈው መልእክት ‹‹ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ሆይ ንብረታችሁን ቤታችሁ አታስቀምጡ፡፡ በተለይ ገንዘብና ጌጣ ጌጥ ካስቀመጣችሁ ፖሊሶቹ መጥተው ይወስዱባችኋል›› ብሏል፡፡ የሳኡሲ አረቢያ መንግስት ዛሬ አስር ቀን ለሞላው ለዚህ በኢትዮጵያዊያን ላይ ላነጣጠረው የእስር ዘመቻ ምንም የሰጠው ምክንያት የለም፡፡ ጋዜጣውም ለባለስልጣናት ኢሜይል ቢልክም አልመለሱለትም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ከፍተኛ የባለስልጣናት ልኡክ ከቀናት በፊት ወደሳኡዲ አረቢያ መላኩን መንግስታዊ ሚዲያዎች ቢዘግቡም ውጤቱን አላሳወቁም።