የአለም ጤና ድርጅት ሳይንቲስቶች ኮቪድ 19 ወረርሽኝን በተመለከተ በቻይና ላይ ያደረጉትን ምርመራ ውጤት ዛሬ ይፋ አድርገዋል

የአለም ጤና ድርጅት ሳይንቲስቶች ኮቪድ 19 ወረርሽኝን በተመለከተ በቻይና ላይ ያደረጉትን ምርመራ ውጤት ዛሬ ይፋ አድርገዋል፡፡

በዚህ መሰረት ቻይና ወረርሽኙን ለአለም ከማሳወቋ በፊት ቫይረሱ በአገሪቱ ውስጥ ተዛምቶ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ ይህንን የምርመራ ቡድን የመሩ ዶክተር ፒተር ኢምባርክ እንዳሉት ከዲሴምበር 2019 በፊት ቢያንስ አስራ ሶስት አይነት የቫይረሱ ዝርያዎች በውሀን ከተማ ውስጥ ነበሩ፡፡ ቻይና ይህን ቫይረስ ካሳወቀችበት ዲሴምበር 2019 በፊት ወደአንድ ሺ ያህል ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው እንደነበር ማረጋረጡን የጠቀሰው ይህ የምርመራ ውጤት በወቅቱ ግን ከቻይና ሪፖርት የተደረገው 174 እንደነበር አውስቷል፡፡

ዶክተር ኢምባርክ ለሲኤንኤን ዛሬ በሰጡት መግለጫ ‹‹ከዲሴምበር በፊት ቫይረሱ በውሀን ተስፋፍቶ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ ግኝት ነው›› ብለዋል፡፡ ይህ የዛሬው መግለጫ ዶክተሩ ከዚህ ቀደም ከሰጡት ጋር የሚጣረስ እንደሆነ ዴይሊ ሜይል አስረድቷል፡፡ ከዚህ ቀደም እኚሁ ዶክተር ‹‹ቫይረሱ ከዲሴምበር 2019 በፊት አልተከሰተም›› ብለው መናገራቸውንም አውስቷል፡፡ እንደዴይሊ ሜይል ዘገባ ቻይና ቫይረሱ ተከስቶ ደብቃ እያለ የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተሩ ቴዎድሮስ አድሀኖም ሲከራከሩላት እንደነበርም አስረድቷል፡፡ ይህንንም ያደረጉት በቻይና እርዳታ ወደስልጣን ስለወጡ እንደሆነ ጨምሮ ዘግቧል፡፡