በዋሽንግተን ዘጠኝ ተቃዋሚዎች የፈጠሩት ጥምረት በህወሀት የታቀደው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ጥረት አንዱ አካል መሆኑን አምባሳደር ፍፁም አረጋ ገለፁ፡፡
(ዘ-ሐበሻ) በዋሽንግተን ዘጠኝ ተቃዋሚዎች የፈጠሩት ጥምረት በህወሀት የታቀደው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ጥረት አንዱ አካል መሆኑን አምባሳደር ፍፁም አረጋ ገለፁ፡፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍፁም አረጋ ከስፑትኒክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህ የስምምነት ፊርማ ህወሀት የጀመረውን አገርን የማፈራረስ ጥረት መቀጠሉን ከማሳየት ውጭ ምንም ትርጉም የሌለው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ንግግራቸውን ሲቀጥሉም ‹‹እነዚህ ጥምረት ፈጥረናል ብለው የተፈራረሙት ግለሰቦች በአንድ የቀድሞ የህወሀት ዲፕሎማት የሚመሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የፖለቲካ ወይንም ወታደራዊ ቡድን እንዳላቸው ምንም ማስረጃ የለም፡፡ ከቀድሞው የህወሀት አምባሳደር በስተቀር ሌሎቹ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ማህበረሰብ አንዳቸውም አይታወቁም›› ብለዋል፡፡
አምባሳደር ፍፁም ስለዚህ ስምምነት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጠይቀው እንደነበር አውስተው ንግግራቸውን ሲቀጥሉም ‹‹ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለእነዚህ ግለሰቦች ምንም እንደማያውቁ ተነግሮኛል፡፡ ጉዳዩን የሰሙትም ከሚዲያ መሆኑን ገልፀውልኛል›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የአሜሪካ መንግስት እንዲህ አይነት ስብሰባ በአገሩ ውስጥ ሲከናወን ዝም ብሎ መመልከቱ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸውም አምባሳደሩ ለስፑትኒክ ገልፀዋል፡፡