ትሪሊስት ‹‹ብላክ ሂስትሪ መንዝ›› በሚል አምድ የጥቁሮች ታሪክ ወር በማስመልከት በዋሽንግተን ዲሲ ስለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ አንድ ዘገባ አቅርቧል
ትሪሊስት ‹‹ብላክ ሂስትሪ መንዝ›› በሚል አምድ የጥቁሮች ታሪክ ወር በማስመልከት በዋሽንግተን ዲሲ ስለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ አንድ ዘገባ አቅርቧል፡፡ ዋሽንግተን ዲሲ የበርካታ ስደተኛ ማህበረሰቦች መኖሪያ ከተማ ቢሆንም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ የጠቀሰው ዘገባው በተለይ ትንሿ ኢትዮጵያ በሚባለው ሰፈር በርካታ የኢትዮጵያዊያንን ሬስቱራንቶችንና ሱቆችን ማግኘት እንደሚቻል አስታውቋል፡፡
ከኢትዮጵያ ውጭ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚኖሩት በዋሽንግተን ዲሲ እንደሆነ ገልፆም በተጨማሪም በሲልቨር ስፕሪንግ፣ ሜሪላንድና አሌክሳንድሪያ እንዲሁም ቨርጂኒያ በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊያንን በብዛት እንደሚኖሩ አስረድቷል፡፡
ዘገባው በዚህ ዙሪያ ሰፋ ያለ ትንታኔ ካቀረበ በኋላም በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች መካከል በምግብ አብሳይ ሼፎች የመረጡትን ዘርዝሯል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ በመጀመሪያ የተቀመጠው የሼፍ ኤልያስ ታደሰ ‹‹ሜላንዥ›› ነው፡፡ በዚህ ሬስቱራንት የዶሮ ወጥ ሳንድዊችና ቅቅል መሰል የፈረንሳይ ምግብ እንደሚገኝ ያስረዳው ዘገባው ይህ ሬስቱራንት በሙሉ አቅሙ ስራ የሚጀምረው በዚህ አመት እንደሆነም አስታውቋል፡፡ በቀጣይነት ዘገባው ያስቀመጣቸው ኢትዮፒክ፣ ፋሚሊ ኢትዮጵያን ሬስቱራንት፣ ፀሀይ፣ ሀበሻ ማርኬት፣ ጨርጨር፣ መአዛ፣ የሺ ክትፎ፣ ዘነበች፣ ቤተሰብና ሞታውን ስኩዌር ፒዛ ሬስቱራንቶችን ነው፡፡