“እንተዋወቃለን ወይ” አቅራቢ የነበረችው አርቲስት ሃና ዮሃንስ ከኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጣብያ መልቀቅዋን በይፋ ተናገረች

         “እንተዋወቃለን ወይ” አቅራቢ የነበረችው አርቲስት ሃና ዮሃንስ ከኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጣብያ መልቀቅዋን በይፋ ተናገረች።  ተወዳጅዋ ተዋናይ ሃና ዮሃንስ ይህንን የገለጸችው ዛሬ ማለዳ በግል የዩቲዩብ ቻናልዋ በለቀቀችው የግማሽ ሰዓት መልዕክትዋ ነው።  

         ሃና ከኢቢኤስ የለቀቀችበትን ምክንያት በስፋት አብራርታለች። ዋነኛ ምክንያትዋ ከዚህ ቀደም ውስጥ ለውስጥ ሲነገር የነበረው የማህተብ ጉዳይ መሆኑን የገለጸችው አርቲስት እምነት የማንነት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑን ሳትጠቅስ አላለፈችም።  ለሞያዋ ስትል ሳትፈልግ ያደረገችው ጉዳይ ህሊናዋን እንደወቀሳት እና ለዚህም ተግባርዋ ይቅርታ መጠየቅ እንደሚገባት ተናግራለች።

         አርቲስት ሃና ከኢቢኤስ አስተዳደር የምትፈልገው ነገር እንደሌለ ገልጻለች። ግን ተቋሙ ካሳ የሚከፍለኝ ከሆነ “ሕዝብን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ” ይክፈለኝ ብላለች። እምነትን በተመለከተ  የኢቢኤስ ጣብያ ዋና ዳይሬክተር የሆነችው ወ/ሮ ማክዳ ቅሬታ እየደረሰባት እንደሆነ ውስጥ አዋቂ ምንጮችን ጠቅሰን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። “እንተዋወቃለን ወይ” ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ ታዳሚዎችን ሽልማታቸውን የሚያገኙት ብዙ ከተጉላሉ በኋላ መሆኑንም መዘገባችን ይታወሳል። ሃና ዮሃንስ በዛሬው መልዕክትዋ ይህንን አስረግጣለች።