‹‹አንድን ነገር በጠመንጃ አፈሙዝ ከቀየርከው ያ ነገር የሚቀየረው በጠመንጃ አፈሙዝ ይሆናል›› – ኦጂዬ አካኒና ባለቤቱ አቻን ኦጋላ በቴክሳስ

(ዘ-ሐበሻ ዜና ) ‹‹ኦጂዬ አካኒና ባለቤቱ አቻን ኦጋላ በቴክሳስ ዋና ከተማ ኦስቲን አምስት ልጆቻቸውን እያሳደጉ የሚኖሩ ቢሆንም የትውልድ አገራቸው ሁኔታ ሁሌም ያሳስባቸዋል፡፡›› በማለት ኦስቲን ዴይሊ ሄራልድ የዛሬ ዘባውን ጀምሯል፡፡ ሲቀጥልም ኦጂዬ ወደአሜሪካ ከመሰደዱ በፊት የኖረባት እናት አገሩ ሌላ ዙር ግጭት ውስጥ መግባቷ በታሪክ መጥፎ ጠባሳ እንዳያሳርፍ ስጋት እንደገባው አስረድቷል፡፡ ኦጂዬ ለጋዜጣው ሲናገር ‹‹አንድን ነገር በጠመንጃ አፈሙዝ ከቀየርከው ያ ነገር የሚቀየረው በጠመንጃ አፈሙዝ ይሆናል›› ብሏል፡፡

ጨምሮም ‹‹ይህ የአሁኑ ጦርነት የሚደረገው እኔ እንደሚገባኝ አብይ ለማምጣት እየሞከረ ባለው ለውጥ የተነሳ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ለውጥ እነዚህ ጦርነት የከፈቱት ሰዎች ደስተኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ በጣም የሚያበሳጨው ደግሞ አሜሪካ የእነሱን ትርክት ብቻ በመቀበል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሱትን ስቃይ እንዲያስፋፉ እድል እየፈጠረላቸው መሆኑ ነው፡፡ እኔ የኢትዮጵያን መንግስት መደገፍ እንዳለብንና ለሴናተሮችም ይህንን እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረብ እንዳለብን ይሰማኛል›› በማለት አስረድቷል፡፡ እንደዘገባው ኦጂዬ የግጭትን መጥፎ ውጤት በቅርበት ያውቀዋል፡፡ በወጣትነቱ ኢትዮጵያን ለቆ ወደኬንያ የተሰደደው ሁለት ቤተሰቦቹ በመገደላቸው ነበር፡፡ ታላቅ ወንድሙ በታናሽ ወንድሙ ፊት በታጣቂዎች የተገደለ ሲሆን ይህም የተፈፀመው የአጎታቸው ግድያ ሀዘን ሳይወጣላቸው ሁለት አመት ሳይሞላ ነበር፡፡ ባለቤቱ አቻንም ብትሆን በርካታ ዘመዶቿን በአገር ቤት በተፈጠረ ግጭት ያጣች ናት፡፡

 

ኦጂዬ መግለጫውን ሲቀጥል ‹‹እኛ በርካታ ዘመዶቻችን በኬንያ ስደተኞች ካምፕ የሚገኙ ሲሆን በየጊዜው እንረዳቸዋለን፡፡ እኛ በሀብታም አገር ውስጥ የምንኖር በመሆናችን ዘመድ አዝማዶቻችንን ማስተማር ይጠበቅብናል፡፡ አሁን በአገራችን ውስጥ ያለው ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ከአመት ወይንም ከሁለት አመታት በኋላ በፊት የነበረው አይነት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወደዚያ አይነት ሁኔታ መመለስ አይኖርባቸውም፡፡ በበኩሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ያልተፈፀሙ ድርጊቶችን በማከናወናቸው እወዳቸዋለሁ፡፡›› ካለ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጡ በቀስታ እየተጓዘ መሆኑን ገልፆ አገሪቱ ግን በትክክለኛ መንገድ እየተራመደች እንደሆነ እንሚያስብ አስታውቋል፡፡ ባለፈው አመትና በዚህ አመት ወደኢትዮጵያ በመሄድ ቆይታ ያደረገው ኦጂዬ የአብይ መንግስት ሙስናን በመቀነስ፣ በርካታ ሴቶችን ወደስልጣን በማውጣትና በአስተሳሰባቸው ብቻ በአሸባሪነት ተፈርጀው እስር ቤት የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት ረገድ ያደረገውን ስራ ጠቅሷል፡፡ ለአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ትልቅ እንቅፋት የሆነው ህወሀት መሆኑን የሚጠቅሰው ኦጂዬ ይህንን ድርጅት በፍጥነት ማጥፋት ካልተቻለ የባሰ ጥፋት እንደሚያስከትልም ያስረዳል፡፡

በዚህ ጥፋት ውስጥ ከሚጎዱት ውስጥ ጋምቤላ ክልል እንደሚሆን ያስታወቀው ኦጂዬ ያለፈው መንግስት በዚህ ረገድ በርካታ መጥፎ ድርጊቶችን አስቀምጦ ማለፉን እንዳስረዳ ጋዜጣው ዘግቧል፡፡