በሰዎች ዝውውር ተጠርጣሪ የሆነው ግለሰብ ባለፈው ወር ከኢትዮጵያ እስር ቤት አምልጧል መባሉ አነጋጋሪ ሆነ

(ዘ-ሐበሻ ዜና) በሰዎች ዝውውር ተጠርጣሪ የሆነው ግለሰብ ባለፈው ወር ከኢትዮጵያ እስር ቤት አምልጧል መባሉ አነጋጋሪ መሆኑን አይሪሽ ታይምስ ዛሬ ዘግቧል፡፡ አሁን በአየርላንድ የምትኖርና ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አንዲት ሴት እንደተናገረችው እሷም በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደአውሮፓ እወስዳችኋለሁ ብሎ ሲያዘዋውር የነበረው ኤርትራዊው ኪዳኔ ዘካሪያስ ሀብተማሪያም ተጎጂ ናት፡፡

በሊቢያ ውስጥ በሚገኘው የዚህ ግለሰብ መጋዘን ውስጥ ለአንድ አመት መታሰሯንም ተናግራለች፡፡ ያኔ የታሰረችው አምስት ሺህ ዶላር እንድታመጣ ተጠይቃ እንደነበር ያወሳችው ይህች ሴት በመጋዘኑ ውስጥ ብዙዎች ሲደበደቡና ሲሰቃዩ እንደነበርም ገልፃለች፡፡ ሁሉም የሚሰቃዩት ገንዘብ እስኪከፍሉ ድረስ እንደነበርና ገንዘቡን ቤተሰቦቻቸው ከከፈሉላቸው በሜዲትራኒያን ባህር አንድ ጀልባ ላይ እንደሚጫኑም አስረድታለች፡፡

ይህ ግለሰብ ባለፈው አመት መጀመሪያ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር መዋሉን ስትሰማ ፍትህ ያገኛል በሚል ተደስታ እንደነበር ለጋዜጣው ተናግራለች፡፡ ይሁንና ይህ በሰዎች ዝውውርና ኮንትሮባንድ ስምንት ክሶች የቀረበበት ተጠርጣሪ ፍርድ ሳይሰጠው ማምለጡን መስማቷን ገልፃለች፡፡

እንደጋዜጣው ዘገባ ኪዳኔ ፌብሩዋሪ 18 ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ለሽንት ብሎ ከሄደ በኋላ የእስረኛ ልብሱን ቀይሮ አምልጧል፡፡ በርካታ በእሱ ላይ የሚመሰክሩ ሰዎች በአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ተገኝተው እንደነበርም ጨምሮ አስታውቋል፡፡ ከእነዚህ ምስክሮች አንዱ የሆነው ዳንኤል አያኖ ለጋዜጣው እንደገለፀው የግለሰቡ ማምለጥ በጉዳዩ ላይ አለም አቀፍ ትኩረቱ አነስተኛ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡