የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አነጋጋሪ ጥያቄ ሆኗል

(ዘ-ሐበሻ ዜና) የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሰኞ ኬንያ እገባለሁ ብለው አስነግረው ዛሬ ሮብ ናይሮቢ ደርሰዋል፡፡ ሚኒስትሩ በዚህኛው ጉብኝታቸው ሁለት ቀናት ብቻ  ይዘግዩ እንጂ ወደአፍሪካ ለመሄድ ካቀዱ በርካታ ወራትን ከማስቆጠራቸው አንፃር መዘግየት አዲሳቸው አይደለም፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አፍሪካን እንደሚጎበኙ በመጀመሪያ ያስነገሩት በነሀሴ ወር ነበር፡፡ ይሁንና ሳይታሰብ ታሊባን መላው አፍጋኒስታንን በመቆጣጠሩ ጉብኝቱን ለማራዘም ተገደዋል፡፡ ዛሬ ሞልቶላቸው ናይሮቢ ሲደርሱ የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይቺሊ ኦማሞ በአየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ በዚህም ከሰሀራ በታች ጉብኝት ያደረጉ የመጀመሪያው የባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን ለመሆን ችለዋል፡፡ የብሊንከንን ይህንን ጉብኝት መስሪያ ቤታቸው የአሜሪካንንና የአፍሪካን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ አስመስሎ ቢያቀርበውም በርካቶች ግን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ አሜሪካ እያከናወነች ያለችው ዲፕሎማሲያዊ ጫና አንዱ አካል አድርገው ተመልክተውታል፡፡

አሜሪካዊያን ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ከፍተኛ ማሳሰቢያ እየሰጠ ያለው መስሪያ ቤታቸው የኢትዮጵያን ግጭት እያጦዘ ባለበት ወቅት ብሊንከን ወደአፍሪካ መምጣታቸው እርግጥም አላማቸውን ቁልጭ አድርጎ ያመላክታል፡፡ በተለይ ደግሞ ጉብኝት የሚያደርጉት በኬንያ፣ ናይጄሪያና ሴኔጋል መሆኑ የአጋጣሚ ሳይሆን ሆነ ተብሎ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲያያዝ ተፈልጎ የተደረገ ነው፡፡ ምክንያቱም የሶስቱም አገራት መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአለ ሲመት ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ የተገኙ ናቸው፡፡ በኬንያ ከፕሬዝደንት ኬንያታና ከሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር አጀንዳው ባልታወቀ ጉዳይ ላይ ሲመካከሩ ሁለት ቀናት የሚቆዩት ብሊንከን ቀጣይ ማረፊያቸውን ናይጄሪያ እንደሚያደርጉ የወጣላቸው መርሀ ግብር ያመለክታል፡፡ በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ተገኝተው አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ፖሊሲ በተመለከተ ንግግር እንደሚያሰሙ መርሀ ግብሩ ያስቀመጠ ሲሆን ይህ ንግግርም የባይደን አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአፍሪካ ላይ የያዘውን አቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ብሊንከን በመጨረሻም በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ይህንን ጉብኝታቸውን የሚያጠናቅቁ ይሆናል፡፡ በናይጄሪያ ቆይታቸው አንቶኒ ብሊንከን በሚያደርጉት ንግግር ላይ የአሜሪካ ፖሊሲ በአፍሪካ ላይ መሰረት የሚያደርገው ዲሞክራሲን እንደሆነ እንደሚገልፁ ይጠበቃል፡፡ በተለይም ባለፈው አመት ብቻ በአፍሪካ ውስጥ በጊኒ፣ በቻድና በማሊ የተከናወኑትን የተሳኩ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቶች እንደሚያወግዙም ይጠበቃል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲያብብ በስፋት የምትሰራ ስለመሆኑ ዲስኩር ያሰማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የፖለቲካ ታዛቢዎች ገልፀዋል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ በማሰብ በፌዴራል መከላከያ ሰራዊቱ የሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛና የታቀደ ጥቃት የፈፀመውን ህወሀትን የአሜሪካ መንግስት እየደገፈ መቆየቱንና አሁንም ድጋፉን መቀጠሉን ፖሊሲው በምን እንደሚመለከተው ታዛቢዎችን ግራ አጋብቷቸዋል፡፡

ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባላት ኢትዮጵያ በአብዛኛው ህዝብ ፍላጎት የተመረጠውን መንግስት እየተቃወመ ያለውና ከስልጣን ለማውረድ ጥረት የሚደርገው አሜሪካ መንግስት ስለዲሞክራሲ እንዴት በድፍረት ሊናገር ይችላል የሚለውም አነጋጋሪ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ሌላው አነጋጋሪ የሆነው ስለኢትዮጵያ ጉዳይ በቀጥታ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መነጋገር እየተቻለ በጎን ዞሮ ከሌሎች አገራት ጋር ምክክር ማድረጉም የአንዲትን ሉአላዊ አገር ክብር መዳፈሩ ነው ብለዋል ታዛቢዎቹ፡፡