የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከጋዜጠኞች ጋር አስገራሚ ፍጥጫ ገጠማቸው

(ዘ-ሐበሻ ዜና) ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ ትላንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የሰብአዊ እርዳታው እንቅስቃሴ መገደብ እንደሌለበትና እርዳታ የጫኑ መኪናዎች ወደትግራይ ክልል ሊተላለፉ እንደሚገባ አበክረው አሳስበዋል፡፡ እነዚህ መኪናዎች እንዲጓጓዙ የኢትዮጵያ መንግስት መፍቀድ እንዳለበትም ጠይቀዋል፡፡ ስለእርዳታው ሁኔታ ተጠይቀው ይህንን መሰል ምላሽ በመስጠት ላይ የነበሩት ኔድ ፕራይስ ቀጠል አድርገው አጀንዳ በመቀየር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ አሜሪካን እንዳሳሰባት ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ክፍት ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አሜሪካዊያን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አውስተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በጣም ብዙ አውሮፕላን ስላለ አሜሪካዊያን እንዲወጡ ያሳሰቡት ቃል አቀባዩ ይህን ጉዳይ የሚከታተለው ቢሮ የስራ ሰአቱን በመጨመር በሳምንት ሰባት ቀናት መስራት መጀመሩንም ገልፀዋል፡፡ ወደአገራቸው ለመመለስ ለሚፈልጉ አሜሪካዊያን የአውሮፕላን ትኬት በብድር ኤምባሲው መቁረጥ እንደጀመረም አስረድተዋል፡፡ ይህንን ከዘረዘሩ በኋላም የአፍጋኒስታን አይነት ሁኔታ እንዳይከሰት አሜሪካዊያን ባለው የመንገደኞች አውሮፕላን አማራጭ መውጣት እንዳለባቸው ገልፀው እስከመጨረሻው ሰአት መቆየት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ ከጋዜጠኞች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ያስገባቸውም ይህ ገለፃቸው ነበር፡፡

ከጋዜጠኞቹ አንዱ እዚህ ጉዳይ ውስጥ አፍጋኒስታንን መጥራት ለምን እንዳስፈለገ የሚያመላክት ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፡፡ ኔድ ፕራይስም ያለው ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆኑን ከጠቀሱ በኋላ በኦባሳንጆና በአጋሮች በኩል የደህንነት ሁኔታውን ወደቀድሞ ለመመለስ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ይህ ጥረት ለአሜሪካዊያን ዋስትና የሚሰጥ ባለመሆኑና በመላው አለም ለሚገኙ አሜሪካዊያን ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ የሚሰጡ በመሆኑ ማሳሰቢያውን መስጠታቸውን አመልክተዋል፡፡ ይህ ምላሻቸው ግን በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞችን  የበለጠ ግራ የሚያጋባ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የተለያዩ ጋዜጠኞች ‹‹እኛ ያልነው ይህ ጉዳይ ከአፍጋኒስታን ጋር ምን ያገናኘዋል? ነው›› በማለት አፋጠዋቸዋል፡፡ አንዱ ጋዜጠኛም ‹‹ከአሜሪካ ጋር ለሀያ አመታት በጦርነት ውስጥ ከቆየችው አፍጋኒስታን ጋር ኢትዮጵያን እንዴት ማመሳል ይቻላል?›› በማለት ግራ በመጋባት መንፈስ ጠይቋቸዋል፡፡ እሳቸው ግን የተፈጠረባቸውን ፍጥጫ በፈገግታ ለመሸፈን ሞክረው ‹‹እኛ ሁሌም በየእለቱ የምንናገረው ስለአሜሪካዊያን ነው›› የሚል ከጥያቄው ጋር የማይሄድ መልስ ሰጥተው ነበር፡፡ ይህ ግን ከቀጣዩ ፍጥጫ አላዳናቸውም፡፡ አንዱ ጋዜጠኛ ‹‹አሜሪካ በወታደራዊ አውሮፕላን አሜሪካዊያንን ከኢትዮጵያ ልታስወጣ ነው እያሉን ይሆን?›› ሲል ሌላ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡

ኔድ ፕራይስም ‹‹እኔ ያልኩት እንደአፍጋኒስታን አይነት የተሳሳተ ግምት እንዲኖር አንፈልግም ነው›› ሲሉ መልሰው ነበር፡፡ ጋዜጠኛውም ‹‹በአፍጋኒስታን የተከሰተው ጉዳይ በአሜሪካ ታሪክ ከዚህ ቀደም ያልተፈጠረ ልዩ ክስተት እንደሆነ ተናግረው ነበር እኮ›› ሲል አፋጧቸዋል፡፡ ቃል አቀባዩም ‹‹በታሪክ ውስጥ ልዩ የሆነ ክስተት በየትኛውም ቦታ ሊደገም ይችላል›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ጭቅጭቁ እንዲቋረጥ ለሌላ ጋዜጠኛ እድል ሰጥተዋል፡፡