በዳውንት ወደ በታች ጋይንት ቆርጦ ሊመጣ የነበረው የሕወሓት ኃይል ተመታ

(ዘ-ሐበሻ ዜና) አሸባሪው እና ወራሪው የሕወሓት ኃይል በጋሸና መስመር ያለውን የኢትዮጵያን ኃይሎች አሰላለፍ ለማዛባት በዳውንት በኩል ቆርጦ ወደ ታች ጋይንት ለመግባት ሙከራ እያደረገ መሆኑን ከቀናት በፊት በዘ-ሐበሻ ዜና ዘግበን ነበር።

ይርጋ ሲሳይ

ዛሬ የደቡብ ጎንደር የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ይህን አረጋግጠው ከሰሞኑ በዳውንት መስመር አድርጎ በታች ጋይንት ወረዳ በኩል ቆርጦ ለመግባት ሙከራ ማድረጉን ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ሕወሓት ይህን ይሞክር እንጂ “ሕዝቡንና የታጠቀውን ኀይል በማነቃነቅ የጠላትን እንቅስቃሴ መገደብ እንደተቻለና ጠላትም ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን” አቶ ይርጋ ገልጸዋል።

የወገን ጥምር ጦር በቅንጅት ባካሄዱት ውጊያ ከፍተኛ ድል ማስመዝገባቸውንም የተናገሩት አስተዳዳሪው በዚህም የወገን ጦር ገዢ ቦታዎችን መያዝ ችሏል ሲሉ ገልጸዋል።

ሕወሃት በዳውንት አካባቢ ንጹሃን የሕክምና ባለሙያዎችን ጭምር መረሸኑን በዘ-ሐበሻ ዜና ዘግበን ነበር።

Comments are closed.