የዘ-ሐበሻ የዕለቱ 9 አጫጭር ዜናዎች

1. የዋግ ህምራ ሰቆጣ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁእ አቡነ በርናባስ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተሰማ፡፡ አደባባይ ሚዲያ እንዳስታወቀው ብፁእነታቸው ታፍነው ስለመወሰዳቸው ቢነገርም ምንም ችግር እንዳላጋጠማቸው ከምንጮቹ ሰምቷል፡፡ በአካል ጳጳሱን ያገኙ ሰዎችን ምስክርነት ማግኘቱንም አስረድቷል፡፡ ብፁእነታቸው የድጓ፣ የቅኔ፣ የዝማሬ መዋስት፣ የሀዲስ ኪዳንና የብሉይ ኪዳን ሊቅና የትህትና መምህር እንዲሁም የፀሎት አባት መሆናቸውንም አውስቷል፡፡ 

2. የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከመጪው ሰኞ አንስቶ በአፍሪካ ሶስት አገራት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለፀ፡፡ የሚጎበኟቸው አገራትም ኬንያ፣ ናይጄሪያና ሴኔጋል ናቸው፡፡ የእነዚህ ሶስት አገራት መሪዎች በመስከረም ወር መጨረሻ በተከናወነው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአለ ሲመት ላይ መገኘታቸው ይታወቃል፡፡

3. ኢትዮጵያ ሁለተኛው የቴሌኮም ተቋም በሚቀጥለው የፈረንጆች አመት የመጀመሪያ ሩብ አመት ስራ ይጀምራል የሚል ግምት እንዳላት አስታወቀች፡፡ ሳፋሪ ኮም በኢትዮጵያ ሁለተኛው የቴሌኮሚኒኬሽን ተቋም ለመሆን 850 ሚሊዮን ዶላር ከፍሎ ንግድ ፈቃድ ማግኘቱ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ ዛሬ በኦንላይን ኮንፈረንስ ላይ እንደተናገሩት ሳፋሪ ኮም አሁን ከቻይናው ሁዋዊ ጋር የኔትወርክ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡  ድርጅቱ በሞባይል ገንዘብ ማስተላለፍ ስራ ላይ እንዲሰማራ የሚያስችለውን ፈቃድ ከብሄራዊ ባንክ ለማግኘት አስፈላጊውን መስፈርት እያጠናቀቀ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ አቶ ብሩክ እንደተናገሩት የኢትዮ ቴሌኮምን 40 ፐርሰንት ድርሻ ለመሸጥም በሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ያለው ግጭት በዚህ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩን አመልክተዋል፡፡ 

4. አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ዜጎቿ ስለመታሰራቸው በዜና ማሰራጫዎች መስማቷ እንዳሳሰባት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ተናገሩ፡፡ ቃል አቀባዩ ጨምረውም በጉዳዩ ላይ መንግስትና በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተነጋገሩበት እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ (ሮይተርስ)

5. የፊሊፔንስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዜጎቹ ወደኢትዮጵያ እንዳይሄዱ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል፡፡ ሚኒስትሩ ትላንት ምሽቱን ባወጣው መግለጫ እስካለፈው አመት ጥር ድረስ ስምንት መቶ ፊሊፔናዊያን ይኖሩ እንደነበር ገልፆ አሁን ምን ያህል እንዳሉ ባይጠቅስም ቀሪዎቹን ማስወጣትን መንግስት ቅድሚያ እንደሚሰጠው አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ፊሊፔናዊያን አንዳች ድጋፍ ከፈለጉ በግብፅ የሚገኘውን የፊሊፔንስ ኤምባሲ ወይንም በአዲስ አበባ ያሉትን ቆንስላ እንዲያነጋግሩም አሳስቧል፡፡ (ማኒላ ታይምስ) 

6. አንድ የሀምሳ አመት ጣሊያናዊ የእርዳታ ሰራተኛ በኢትዮጵያ ውስጥ መታሰሩን ላ ሪፐብሊካ የተሰኘው የሮም እለታዊ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ አልቤርቶ ሊቮኒ የተባለው ይህ ጣሊያናዊ ሳለሲያን የተሰኘው የእርዳታ ድርጅት ውስጥ የሚሰራ እንደሆነም ዘገባው አስረድቷል፡፡ የዚህ በትግራይ ክልል በስፋት የሚንቀሳቀሰውና ዶንቦስኮ የተሰኘ ትምህርት ቤትን የሚያስተዳድረው ድርጅት አባላት መካከል የተወሰኑት በአዲስ አበባ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህም ለእስር የተዳረጉት ለህወሀት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በማሰብ ከአዲስ አበባ ወደትግራይ ገንዘብ ልካችኋል በሚል ተጠርጥረው እንደሆነ መገለፁ ይታወቃል፡፡ ጣሊያናዊው ሊቮኒም ከእነዚህ መካከል አንዱ እንደሆነ ዘገባው አስረድቷል፡፡ ጉዳዩን በአዲስ አበባ የሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲና በሮም ያለው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እየተከታተሉት እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡

7. ሳኡዲ አረቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በቅርበትና በስጋት እየተከታተለችው መሆኑን እንዳስታወቀች ሳኡዲ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡ የሳኡዲ አረቢያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ ጠቅሶ የዜና ምንጩ እንዳስታወቀው የሳኡዲ መንግስት ተኩስ አቁም እንዲደረግና ሁሉም አካላት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግለት ያሳሰበው መግለጫው የእርዳታ ሰራተኞች ስራቸውን ለማከናወን እንዲፈቀድላቸውም ጠይቋል ተብሏል፡፡   

8. የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ዛሬ በኢትዮጵያ የሳኡዲ አረቢያ አምባሳደር የሆኑትን ሳሚ ጃሚል አብዱላሂን በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል፡፡ በወቅቱም ሁለቱ አገራት  በውሀና ኢነርጂ ዘርፍ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ሳኡዲ አረቢያ የኢትዮጵያን የውሀ ዘርፍ ልማት ለማገዝ ሀምሳ ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል መግባቷም ተዘግቧል፡፡

9. በቆዳ ምርቶች ዘርፍ ላይ የተሰማራው የእንግሊዙ ፒቲያርድስ ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግጭት እንቅስቃሴውን እንዳልጎዳው አስታወቀ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ጫማ በማምረት ስራ ላይ የተሰማራው ይህ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለው እንደሆነ ገልፆ እስካሁን ምርቶቹን፣ ስራውንና ሰራተኞቹን በተመለከተ ምንም ተፅእኖ እንዳልገጠመው ገልጿል፡፡ (ለንደን ሳውዝ ኢስት ጋዜጣ)

…….   ከዘሀበሻ ጋር አብረውን ይቆዩ፡፡…….

እናመሰግናለን!!

እውነት ያሸንፋል!!