የታንዛኒያው ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ በእስር ቤት ለሚገኙ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን ምህረት ማድረጋቸውን አስታወቁ

ፕሬዝደንቱ ይህንን የገለፁት ከፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር የነበራቸውን ውይይት ካጠናቀቁ በኋላ ነው፡፡ ማግፉሊ በቴሌቪዥን በተሰራጨ መግለጫቸው ሲናገሩ ‹‹ህገ ወጥ ስደተኛ በመሆናቸው የታሰሩትና አንዳንዶቹም እስከ ሰባት አመት በእስር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈታሉ›› ብለዋል፡፡ ጨምረውም እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ወደአገራቸው ተመልሰው በአገር ግንባታው ላይ እንደሚሳተፉ አስረድተዋል፡፡

ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያኑ እንዲለቀቁ በመወሰኑ ምስጋናቸውን አቅርበው እስረኞቹ ከእስር ከወጡ በኋላ ወደአገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ታንዛኒያ የሚገኘው ኤምባሲ እንደሚቆዩ ገልፀዋል፡፡ ለአንድ ቀን ጉብኝት ዛሬ ታንዛኒያ የተገኙት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሲናገሩም ‹‹ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር ለመስራት ዝግጁ ናት፡፡ ግንኙነታችንን ወደላቀ ደረጃ እናሳድገዋለን›› ብለዋል፡፡

በታንዛኒያ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለያየ ኢንቨስትመንት ላይ እንደተሰማሩ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ199 እስከ 2020 ባለው ጊዜ በታንዛኒያ አስራ ሶስት የኢትዮጵያዊያን ኢንቨስትመንት እንደተመዘገበና ይህም አስራ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ እንደሆነ የገለፀው ሚኒስቴሩ በዚህም ለ677 ታንዛኒያዊያን የስራ እድል እንደተፈጠረ አስረድቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ጉብኝት በታንዛኒያ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ከመሆኑም በላይ የአገሪቱ ጋዜጦችና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሰፊ ቦታ ሰጥተው ዘግበውታል፡፡