የአሜሪካ ስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) አስገራሚ ትንበያ በኢትዮጵያ ላይ አወጣ

(የዘ-ሐበሻ ዜና) በአሜሪካ የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ከሚገኝ መረጃ በየጊዜው የሚወጣው ‹‹ኢንሴኪዩሪቲ ኢንሳይት›› ዛሬ ኢትዮጵያን የተመለከተ ትንታኔና ትንበያውን አቅርቧል፡፡ ትንታኔውን የጀመረው በአዲሱ የተቃዋሚዎች ጥምረት ወደፊት መግፋት የኢትዮጵያ መንግስት ጫና ውስጥ መግባቱን በመግለፅ ሲሆን በህወሀትና በኦነግ ሸኔ እየተደረገ ያለው ውጊያ አላማው በፍጥነት ሁሉንም ወደአዲስ አበባ የሚያስገቡ መንገዶች መዝጋት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በዚህም መንግስት በጅቡቲ ወደብ በኩል አቅርቦት እንዳያገኝና ከኤርትራ ደጋፊ ሀይል እንዳያስገባ ለማድረግ ማሰባቸውን ጠቁሞ ወደአዲስ አበባ ያለምንም ችግር ሰተት ብለው ለመግባት ብቸኛ አማራጫቸው እነዚህ ሆነው እንዳገኙትም አስረድቷል፡፡ ባለፉት ቀናት አዲስ አበባንና ጅቡቲን የሚያገናኘው አውራ ጎዳና ከሚገኝበት በስተደቡብ በሚገኘው ሚሌ ከተማ አቅራቢያ ከፍተኛ ውጊያ እየተከናወነ እንደሆነ የህወሀት ደጋፊ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲገልፁ መቆየታቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ የህወሀት አመራሮች ወደሚሊ እየተጓዙ እንደሆነ ከተናገሩ አስር ቀን እንዳለፋቸውም አመልክቷል፡፡ የህወሀት እቅድ ሚሌን ከያዘ በኋላ በድሬዳዋ በኩል የሚያልፈውን የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር በቁጥጥር ስር ማስገባት እንደሆነም ይፋ አድርጓል፡፡

ወደአዲስ አበባ ህወሀትና ኦነግ የሚያደርጉትን ጉዞ በተመለከተ ደግሞ ከኖቬምበር ወር መጀመሪያ አንስቶ ማለትም ላለፉት አስራ አራት ቀናት ወደአዲስ አበባ የማምራት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስረድቷል፡፡ ይኸው በሲአይኤ የሚዘጋጀው መረጃ እንዳለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በደብረ ብርሀንና በሸዋሮቢት በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ ጥበቃ እየደረገ ሲሆን የህወሀት ታጣቂዎች ከጥቂት ቀናት በፊት ማለትም ኖቬምበር ስምንት ወደደብረብርሀን ሊያደርጉት የነበረው የጥቃት ሙከራ በአየር ድብደባ እገዛ ከሽፎ ወደኋላ እንዲሸሹ አድርጓቸዋል፡፡ የታጣቂዎቹ መጣመርና ዲፕሎማሲያዊ ጫናው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ለመደራደር መጠነኛ ክፍተት የፈጠረ መሆኑን ያስረዳው መረጃው የተኩስ አቁም የመፈጠር እድሉ ግን ጠባብ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

መረጃው በመቀጠልም ሁለቱም አካላት በፖለቲካ መፍትሄ ላይ ድርድር ለማድረግ የተለያየ ምክንያት ማቅረባቸውን እንደሚቀጥሉ ትንበያውን አቅርቧል፡፡ ሲአይኤ በዛሬው መረጃው ጥብቅ ሚስጥሮችንና የአሜሪካ መንግስትን አቋምንም ይፋ አድርጓል፡፡ ለዚህ ግጭት አብይ ከስልጣን ካልወረደ የፖለቲካ መፍትሄ ሊመጣ እንደማይችል የገመተው መረጃው፣ አብይ አህመድ በፈቃዱ ስልጣን ሊለቅ ወይንም መፈንቅለ መንግስት ሊኖር እንደሚችልም ትንበያውን አቅርቧል፡፡

በተለይ መፈንቅለ መንግስት ከተደረገ ኦባሳንጆ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚያደርጉትን የድርድር ጥረት ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ተመልሶ ወደስልጣን ለሚወጣው ህወሀት እውቅና ይሰጠዋል የሚል ግምት እንዳለውም አስታውቋል፡፡