የአዲስ አበባ ሕዝብ እየደረሰብኝ ነው ያለውን መገፋት እና ብሶት በአደባባይ ተቃውሞ አሰማ

የአዲስ አበባ ሕዝብ እየደረሰብኝ ነው ያለውን መገፋት እና ብሶት በአደባባይ ተቃውሞ አሰማ

የዘንድሮው የአድዋ ድል በዓል በተለያዩ የኢትዮጵያ ለተሞች በድምቀት ተከብሮ በሰላም ተጠናቋል። በዓሉ በአዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ፤ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ያዘጋጀው በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል። በባህርዳር፣ በጎንደር፣ በደብረማርቆስ፣ በደሴ፣ በአርባምንጭ ፓራዳይዝ ሎጅ ውስጥ፣ በአዋሳ፣ በድሬደዋና በሌሎችም የኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞች ተከብሯል። እንዲሁም በውጥረት ውስጥ በከረመችውም መቀሌ ከተማ 125ኛው ዓመት የአድዋ ድል በዓል በፓናል ውይይት ተከብሯል፡

የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ዙሪያ የተሰባሰቡ በርካታ ፈረሰኞች የተሳተፉበት ደማቅ በዓሉን በመስቀል አደባባይ ያከበረ ሲሆን የአዲስ አበባ ሕዝብ ደግሞ በምኒልክ አደባባይ በድምቀት አክብሮታል።
የዘንድሮው የአድዋ ድል በዓል የአዲስ አበባ ሕዝብ እየደረሰብኝ ነው ያለውን መገፋት እና ብሶቱን በአደባባይ የገለጸበት በዓልም ሆኖ አልፏል። በይገባኛል ስሜት አዲስ አበባን ለራሳቸው ለማድረግ ለሚያስቡትም፤ ታሪክን እነርሱ በፈለጉት መንገድ ለመጻፍ ለሚሞክሩትም የአዲስ አበባ ህዝብ ተቃውሞውን ገልጾላቸዋል።

ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅትም ጀግኖች አባቶች ያስረከቡትን ሃገር እንደሚያስጠብቅ የገለጸ ሲሆን በዓሉ እየደረሰበት ያለውን መገፋት፤ እና ብሶት በአደባባይ የገለጸበት ሆኖ በሰላም ተጠናቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ክልል በመስቀል አደባባይ ይህን በዓል ሲያከብር የባልቻ አባነፍሶን እና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ፎቶ ብቻ መጠቀሙ ቁጣን ቀስቅሷል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር የሆኑት ዶ.ር ሲሳይ መንግስቴ ይህን ካዩ በኋላ ባሰፈሩት ትችት “ማፈርና ማዘን በዚህ አስነዋሪ ድርጊት ፈጻሚዎች ሳይሆን በዶ/ር አብይና አጫፋሪዎቹ ነው። እንዴት ሰው የአድዋን የድል በአል እያከበረ አጼ ምኒልክንና እቴጌ ጣይቱን ወደ ጎን ትቶ በጊዜው ያልነበረውን የዶ/ር አብይን ፎቶ በአደባባይ ይሰቀላል። ይኸ ስሁት ድርጊት ከተረኝነት አስተሳሰብ የሚመጣ ነው የሚባለው በምክንያት መሆኑን ያረጋግጣል።


የዘንድሮው የኦሮሞ ፖለቲከኞች ስሁት እንቅስቃሴ የአምናውን የትህነጎች እብሪት እንዳስታውስ አደረገኝ። አምና በዚህ ወቅት ትህነግ የሚይዘውና የሚጨብጠው ጠፍቶት ስለነበር የትግራይ ቴሌቪዥኖች የአድዋን በአል ሲያከብሩ ከበስተጀርባ የሚታየው ፎቶ የአጼ ዮሀንስ

4ኛ እና የመለስ ዜናዊ ነበር። ለካ ታሪክ ራሱን ይደግማል የሚባለው እውነት ነው።
ይህም ማለት በዚህ አመት በትግራይ የተወሰደውን የህግ ማስከበር ተግባር የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሳይሆኑ ሽመልስ አብዲሳ ወይም ታየ ደንደዓ ናቸው እንደማለት ነው። ለምን ቢባል ግንባር ባይሄዱም በየሚዲያው እየወጡ ተናግረዋልና።


እርግጥ ነው ባልቻ ሳፎ/አባነፍሶ አድዋ ላይ ብቻ ሳይሆን ጣሊያን ከ40 አመት በኋላ ኢትዮጵያን በድጋሜ ለመውረር ሲመጣ ማይጨው ላይ በተደረገ ውጊያ በ80 አመታቸው ተሳትፈዋል አኩሪ መስዋዕትነት ከፍለዋልና ሊታሰቡ ይገባል። ይህም ማለት ግን ከዋና መሪ ልቀው መታየት ይኖርባቸዋል ማለት አይደለም።
ከዚህ ውጭ ዋናውን መሪን ትቶ ተሳታፊውንና በቦታው ያልነበረን ሰው እንዲህ አጉልቶ ማሳየት ከተረኝነት እሳቤ የመጣ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል? እውነቱን ለመናገር ባልቻም ሆኑ ሀብተጊወርጊስ የእምየ ምኒል ግርፎች መሆናቸውን መርሳት የዋህነት ነው የሚሆነው። እንግዲህ ወንድምና እህቶቻችንን ልብ ሰጥቶ ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱና ለጋራ ታሪካችን ተገቢ ዋጋ እንዲሰጡ ከመምከርና ከመገሰጽ በስተቀር ምን ምርጫ አለን።”ብለዋል።

“ዛሬ የአድዋን በአል ብቻ አይደለም ያከበርነው፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው በአማራ ክልል የራያ ባላ ወረዳ የምስረታ ፕሮግራምም ድላችንን ሙሉ እንዲሆን አድርጎታል። ለጊዜው የዚህች አዲስ ወረዳ አካል ያልሆኑ የራያ ጨርጨር ቀበሌዎችም በቅርቡ ወደ ወገናቸው እንደሚቀላቀሉ ተስፋ እናደርጋለን።


የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንደሚባለው ትህነግ በአልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ስሜት ውስጥ ሆኖ ብዙ ሲያግበሰብስ ቆይቶ አሁን ላይ ራሱ በለኮሰው እሳት ተለብልቦ ወልቃይት ጠገዴና ራያን በአስገራሚ ሁኔታ ማጣት ችሏል። በተቃራኒው እንደ ቅድመ አያታቸው ራስ መንገሻ ሁሉ ዋሻ ውስጥ ሆኖ ለማላዘን ተገዷል።


ህዝቡም ነጻ ወጣና የሚፈልገውን ነገር አደረገ። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ? ይህ ስኬት እንዲገኝ አስተዋጽኦ ያደረጋችሁ አካላት ሀሳባችሁ እውን ሆኗልና እንኳን ደስ አላችሁ! በሌላ ፕሮግራም ምክንያት በቦታው ተገኝቼ ደስታየን መግለጽ ባልችልም በሀሳብ አብሬያቸው እንደሆንሁ አረጋግጨላቸዋለሁ።” ብለዋል።