ይድረስ ለአቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ፕሬዚደንት – ከኮሎራዶ የአማራ ማህበር የተላከ

መስከረም ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. (September 18, 2020)

ለአቶ ተመስገን ጥሩነህ – የአማራ ክልል ፕሬዚደንት:-

በአማራ ክልል ለምትገኙ የትላንቱ ብአዴን/አዴፖ የዛሬው ብልፅግና ፖርቲ የመንግስት አመራር አካላት በሙሉ

(PDF) ይህንን ደብዳቤ ስንፅፍላችሁ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ህዝባችን ላይ የሚደረገውን በአለም ውስጥ ከፍተኛ ሰቆቃ የሞላበት የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እየተመለከታችሁ ወይም ከተባባሪነት ያላነሰ ተሳትፎ እያደረጋችሁ በህዝባችን ጫንቃ ላይ እራሳችሁን በማንሰራፋት በምትሰሩት የግፍ ስራ ልባችን ተሰብሮ ነው።

የአማራ ሰፊው ህዝብ፣ በተለይም አርሶ አደሩ በመላው ሀገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ አርሶ እያበላ፣ ሀገሩን ከጠላት እየተከላከለ የመኖር ታሪኩ በእውነት መረጃ የተደገፈ ነው።

ይህ ታላቅ ህዝብ በአማራነቱ ብቻ እየተመረጠ ከስነ ልቦና ጀምሮ የህይወት ማጥፋት ሲፈፀምበት ቀድሞ በወያኔ ካድሬነታችሁ አሁንም በኦነግና ብልፅግና ተላላኪነታችሁ የተጨፈጨፈው ወገናችን የውዱ አማራ ደም በእጃችሁ ላይ ይገኛል።

የአማራ ህዝብ ሳይመርጣችሁ ህዝባችን የራሱ ምድር በሆነው የኦሮሞ ክልል እና ቤንሻንጉል በሚባለው አካባቢ አንገቱና ሰውነቱ ሲቆራረጥ፣ አማራ አይወለድም እየተባለ ለመውለድ የደረሰች እናት ስትገደል፣ ሽል ከእናት ሆድ እየወጣ ሜዳ ላይ ሲጣል አባቶችና እናቶች በአሰቃቂ ሁኔታ በልጆቻቸው ፊት ሲገደሉ፣ ልጆች በወላጆቻቸው ፊት ሲታረዱ እናንተ የአማራ መሪዎች ነን ብላችሁ እንኳን አማራውን ልትከላከሉ፣ ለገዳዮቹ መሪዎች የባህላችንን የክብር ካባ ያለህዝብ ፈቃድ እየሸለማችሁ በአማራው ላይ የሚደረገውን ግድያ ታበረታታላችሁ። ሰሞኑንም በመተከል በአማራ ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋ ቁጭ ብላችሁ ታያላችሁ፣ የተፈናቀለው ህዝብ ወደ ቦታው ተመልሷል በማለት ትዋሻላችሁ ታስዋሻላችሁ።

ስለሆነም ለእናንተ እና ለወካያችሁ የዶ/ር አቢይ መንግስት ከፍተኛ ተቃውሞአችንን እያሰማን

የሚከተሉትን ጥያቄዎችና ጥሪ እናቀርባለን፦

፩ የኦሮሞ እና ቤንሻንጉል ክልል በሚባሉት አካባቢዎች የተጨፈጨፉ ወገኖቻችን መታሰቢያ በፍጥነት በዋና ከተማዎቻችን አዲስ አበባ እና ባህር ዳር እንዲሰራ፣ ለቤተሰቦቻቸውም ካሳ እንዲከፈል

፪ የአሥራት ጋዜጠኞች ስለ ወገናቸው ሰቆቃ ለምን እውነትን ዘገባችሁ ተብለው የታሰሩት እና ስለእውነትም ሲታገሉ የታሰሩ አማራ የፖለቲካ እስረኞችን በአስቸኳይ እንድትፈቱ እንድታስፈቱ።

፫ የታፈኑት የዶምቢዶሎ ተማሪ እህቶቻችንን በሚመለከት ያደረጋችሁትን
ነገር ለአማራ ህዝብ ለመላው ኢትዮጵያና ጉዳዩን በትኩረት ለሚከታተሉ አለም አቀፍ ተቋማት በፍጥነት እንድታሳውቁና ወላጆቻቸውን ማንገላታት እንድታቆሙ፣

፬ የአማራው ሰው ሰራሽ ጥቃት ከላይ ከተገለፁት አካባቢዎች ሌላ በወልቃይት ጠገዴ፣ በደራ፣ በራያ፣ በከሚሴ በሌሎችም የሚካሄድ ሲሆን በተፈጥሮም የጣና እምቦጭና ውሃ ሙላት በፎገራ ያደረሰውን ጉዳት እያያችሁ በቂ እርምጃ ባለመውሰዳችሁ ከፍርድ ተጠያቂነት አትድኑም።

፭ የአማራው ህዝብ በመላ ኢትዮጵያ ከወጣት እስከ አዛውንት ራሱን ለመከላከል የሚይስችለውን የጦር መሳሪያ እንድታስታጥቁ፣ የታጠቀውንም ህጋዊ ፈቃድ እንድትሰጡ (UN Charter VII, Article 51)

፮ የፌዴራል መንግስት የአማራውን ቁጥር በማሳነስ የሚያደርገውን የኢኮኖሚ ስርቆት እንድታስቆሙ

እነዚህን አሁኑ በፍጥነት ማድረግ ካልቻላችሁ የያዛችሁትን ቦታ ለእውነተኛ አማራ የሀይማኖት አባቶች፣ መለዮ ለባሾች፣ የፋኖ ተወካዮች፣ የሴቶች ተወካዮች አስረክባችሁ እንድትለቁ ስንጠይቅ በመላው ኢትዮጵያ እና በአለም ዙሪያ ላለው አማራ የሚከተሉትን ጥሪዎች እናቀርባለን።

፩ በመላው ኢትዮጵያ የምትገኝ ታላቁ የአማራ ህዝብ፣ ሰፊው አርሶ አደር፣ ጀግናው ባለአደራ የአማራ ወጣት፣ አርበኛ አባትና እናቶቻችን፣ ወጣትና ጥበበኛ የአማራ
ሴት ልጆች፣ በልዩ ልዩ ሙያ የተሰማራችሁ መምህራን፣ ሀኪሞች፣ ኢንጅነሮች፣ የመከላከያ ሰራዊት ሀይሎች፣ የቀን ሰርቶ አደሮች እንዲሁም ሌሎች በአንድነት በመነሳት የታወጀብንን የዘር ማጥፋት ዘመቻ genocide ለመከላከል በማናቸውም መንገድ በመደራጀት ራሳችሁን አዘጋጁ

፪ ከኢትዮጵያ ውጪ የምንገኝ መላው የአማራ ህዝቦች ሁሉ ህዝባችንን ከእልቂት ለማዳን በአንድ ጥላ ስር በመሆንና በመሰባሰብ በትግል ስትራቴጂ ውስጥ በእውቀትና በፋይናንስ ለማገዝ እንነሳ

፫ መላው እውነተኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ የአማራው መኖር የኢትዮጵያ መኖር የኢትዮጵያ መኖር የአማራው መኖር መሆኑንም በመረዳት ሀገራችንን ለማጥፋት የተነሳውን የአማራን ዘር ማጥፋት ዘመቻ በጀግነት እንድትቃወሙና ከአማራው ጎን እንድትቆሙ ኢትዮጵያዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የአማራው ደም ፈሶ አይቀርም!!!
አምላክ ትግላችንን ይመራል ህዝባችንንም ያድናል!!! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!

የአማራ ማህበር በኮሎራዶ USA

ግልባጭ

ለክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት

ለክቡር ዶ/ር አቢይ አህመድ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

ጄነራል አደም መሐመድ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም

ለመላው የሃይማኖት መሪዎች

ለኢትዮ 360 ሚዲያ

ለዘ-ሐበሻ ሚዲያ

ለአባይ ሚዲያ

ለሚኒሊክ ሚዲያ

ለቮይስ ኦፍ አሜሪካ

ለፋና ሚዲያ

ለአዲስ ድምፅ ሚዲያ