ከእንግሊዝ ጦር ሀይል የተውጣጡ ወታደሮች ብሪታኒያዊያንን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት በምስጢር ኬንያ መግባታቸው ተዘገበ

Photo: File

(ዘ-ሐበሻ ዜና) ቱ ራፋይልስ ከተሰኘው የእንግሊዝ ጦር ሀይል የተውጣጡ ወታደሮች ብሪታኒያዊያንን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት በተጠንቀቅ ቆመው እየተጠባበቁ መሆኑን ዘ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ ዛሬ ባሰራጨው መረጃ ገልጿል፡፡ እነዚህ ቁጥራቸው ከአንድ መቶ በላይ የሆኑ ወታደሮች በአሁኑ ወቅት በጎረቤት አገር ኬንያ በምስጢር መስፈራቸውን ጋዜጣው ወታደራዊ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ አስረድቷል፡፡ ኬንያ የገቡት እነዚህ ወታደሮች ቁጥራቸው በትክክል ምን ያህል እንደሆነ ምንጮቹ እንዳልነገሩ ያስታወቀው ዘገባው በመቶዎች የሚቆጠሩ ይሆናሉ የሚል ግምት እንዳለም አመልክቷል፡፡ ወታደሮቹ በተጠንቀቅ ቆመው ትእዛዝ እስኪሰጣቸው ድረስ እንዲጠባበቁ እንደተነገራቸው ዘገባው ጨምሮ አስታውቋል፡፡

የእንግሊዝ መንግስት ይህንን ያደረገው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፀጥታ ሁኔታ የከፋ ከሆነ በሚል ግምት መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው የከፋ የሚለው ግምት እውን ከሆነና ብሪታኒያዊያንን በሌላ መንገድ ከኢትዮጵያ ለማስወጣት አማራጭ ከጠፋ እነዚህ ወታደሮች እንደሚሰማሩ ገልጿል፡፡ በካቡል በሺህ የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናዊያንንና ብሪታዊያንን በተመሳሳይ መንገድ የማስወጣት ወታደራዊ ዘመቻ መከናወኑን ያወሱት የጋዜጣው ምንጭ እነዚህ ወታደሮች ኬንያ የተቀመጡትም ይህንን ለመድገም እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ቱ ራፋይልስ የተሰኘው ጦር ሀይል በሰሜናዊ አየር ላንድ የሚገኝ ሲሆን እነዚህ ወታደሮችም የመጡት ከዚያ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ዘ ታይምስ ጋዜጣም የአየርላንድ ከመሆኑ አንፃር ይህ ዘገባ እንዲሰራጭ የተደረገው ከአየርላንድ መንግስት እንደሆነ የፖለቲካ ታዛቢዎች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡

አየር ላንድ በከፍተኛ ደረጃ ለህወሀት ድጋፍ ከሚሰጡ አገራት ግንባር ቀደም ከመሆኗም በላይ በግልፅ ህወሀት ወደስልጣን ተመልሶ እንዲወጣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጭምር አቋሟን ስታሳይ የቆየች አገር መሆኗ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አሁን የአየርላንድ ወታደሮች ኬንያ እንደሰፈሩ አስደርጋ የምታስወራውም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ለማሳሰብና ህወሀትን ለማዳን የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲፈጠር ጫና ለማድረግ እንደሆነ ታዛቢዎቹ ያስረዳሉ፡፡ እንደታዛቢዎቹ ገለፃ በአሁኑ ወቅት የትኛውም አገር ዜጎቹን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት በርካታ የአውሮፕላን አማራጮች ስላሉ በዚያ አሳፍሮ መውሰድ ይቻላል፡፡ የአየር ላንድ መንግስትም ዜጎቹን አሁን ማስወጣት እየቻለ በሚስጥር ወታደሮችን በኬንያ ማስቀመጡን መግለፁ የፖለቲካ ሴራ ውስጥ መዘፈቁን በገሀድ እንዳወጣው ታዛቢዎቹ ገልፀዋል፡፡