የኬንያ አየር መንገድ ወደኢትዮጵያ በሳምንት ሶስት ቀናት ያደርግ የነበረውን በረራ ወደሰባት ማሳደጉን አስታወቀ
(ዘ-ሐበሻ ) የኬንያ አየር መንገድ ወደኢትዮጵያ በሳምንት ሶስት ቀናት ያደርግ የነበረውን በረራ ወደሰባት ማሳደጉን አስታወቀ፡፡ ይህንን ውሳኔ ያደረገውም የመንገደኞች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ እንደሆነ ገልጿል፡፡
የኬንያ አየር መንገድ በሳምንት ተጨማሪ አራት በረራዎችን እያደረገ ያለው በርካታ አገራት ዜጎቻቸውን ከኢትዮጵያ የማስወጣት እንቅስቃሴ ላይ በመሆናቸው ነው፡፡ አየር መንገዱ በዚህ እድል ለመጠቀምና የመንገደኞችን ቀልብ ለመሳብ እስከ ኖቬምበር አስራ ሰባት ለሚጓዙ የአስራ አምስት ፐርሰንት ቅናሽ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ማሳሰቢያ መስጠቱን ተከትሎ የሀሰት ዜና ፋብሪካ የሆነው ሲኤንኤን አዲስ አበባ እንደተከበበች አድርጎ ዘገባ ማሰራጨቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ ዲፕሎማቶችን ስጋት ውስጥ መክተቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ የተነሳም በርካታ አገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ መግለጫ ሲያወጡ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡