በአዲሱ መጠሪያው ሜታ የተባለው ፌስ ቡክ ለኢትዮጵያ ተጠቃሚዎቹ አዲስ መመሪያ አውጥቷል
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በአዲሱ መጠሪያው ሜታ የተባለው ፌስ ቡክ ለኢትዮጵያ ተጠቃሚዎቹ አዲስ መመሪያ አውጥቷል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ የግጭት ስጋት ያለባት አገር እንደመሆኗ መጠን ቅድሚያ ከምንሰጣቸው አገራት ተርታ አስቀምጠናት ቆይተናል›› ሲል የጀመረው መመሪያው ባለፉት ሁለት አመታትም በኢትዮጵያ ውስጥ ጥላቻንና ለግጭት የሚያነሳሱ ይዘቶችን ለመቀነስ ከፍተኛ ወጪ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን አስታውቋል፡፡ አሁን ደግሞ ሁኔታው እየተባባሰ በመምጣቱ የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ተጨማሪ ክልከላዎችን ለመጣል መገደዱን አስረድቷል፡፡
ከእነዚህ መካከል በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጩ ይዘቶች ላይ ገደብ ማስቀመጡን ያስታወቀው የሚገኝበት ሲሆን ከሁለትና ከዚያ በላይ የሼር ሰንሰለት ያላቸውን ፖስቶች የጥላቻ ንግግር ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ግምት እንደሚያጠፋቸው ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ሰዎች ወደአንድ ቦታ ጦር መሳሪያ ይዘው እንዲሄዱ የሚያሳቡ፣ ጦር መሳሪያ እንዲታጠቁና ብቀላ እንዲፈፅሙ የሚጠይቁ ፅሁፎችን እንደሚያጠፋ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትን የሚያነሳሱ ኦነግ ሸኔና አባ ቶርቤ የተባሉ ቡድኖችንና ግለሰቦችን በቅርቡ ማገዱን የገለፀው ሜታ ይህንን እርምጃ በሌሎችም ላይ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡ የጥላቻ ንግግርን በአራቱ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ላይ እያደነ መፈለጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ገልፆም ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን የማጥፋት አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡