ሊዝ ትሮሴል በኢትዮጵያ ጉዳይ ጋዜጣዊ መግለጫ አወጡ

(ዘ-ሐበሻ ዜና) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሴል በኢትዮጵያ ጉዳይ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኢትዮጵያ ውስጥ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተገን በማድረግ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳርና ሌሎችም አካባቢዎች መጠነ ሰፊ እስርና ፍተሻ እየተከናወነ መሆኑ ድርጅታቸውን እንዳሳሰበው ገልፀዋል፡፡ ይህ ከሚከናወንባቸው ውስጥ አብዛኛዎቹ ለህወሀት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ወይንም ከህወሀት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ከሚዲያ መስማታቸውን ያስታወቁት ቃል አቀባይዋ ባለፈው ሳምንት ብቻ ቢያንስ አንድ ሺህ ግለሰቦች ስለመታሰራቸው ሚዲያዎቹ መግለፃቸውን አስረድተዋል፡፡

መግለጫቸውን ሲቀጥሉም እነዚህ እስረኞች በተጨናነቀ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ መታጨቃቸው መዘገቡ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ህግ ስለእስረኞች አያያዝ ያወጣውን ደንብ እንደሚጥስ አስታውቀው እነዚህ እስረኞች ለምን እንደታሰሩ ያልተገለፀላቸው መሆኑን ከሚዲያ መስማታቸውን ጠቅሰውም ተቃውመውታል፡፡ እነዚህን ነገሮች ከዘረዘሩ በኋላም የተመድ ሰራተኞች የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ አስር ሰራተኞችና ሰላሳ አራት በሰብ ኮንትራት የተቀጠሩ ሹፌሮች አሁንም በእስር ላይ እንዳሉና በፍጥነት እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ ወይንም ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብትና የሰብአዊነት ሁኔታ የከፋ ሊያደርገው እንደሚችል የገለፁት ቃል አቀባይዋ አዋጁ ለመንግስት ሰፊ መብት እንደሰጠው ጠቅሰዋል፡፡